
ባሕርዳር፡ ግንቦት 17/2012 ዓ.ም (አብመድ) በምዕራብ ጎንደር ዞን ቋራ ወረዳ የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል የተላለፉ ክልከላዎች ተግባራዊ አለመደረጋቸው ስጋት እንደፈጠረባቸው ነዋሪዎቹ ተናግረዋል፡፡
በወረዳው የተለያዩ ቀበሌዎች ያሉ ነዋሪዎች ለአብመድ እንዳስታወቁት በተለይ በአካባቢው ያለው የትራፊክ እንቅስቃሴ ለቫይረሱ አጋላጭ ነው፡፡ ከቋራ ወደ ገንዳውኃ ሰዎችን በሚያጓጉዙ የሕዝብ ማመላለሻዎች ሕዝቡ እጥፍ እየከፈለ መኪኖቹ ግን በሙሉ አቅም እየጫኑ እንደሆነም በአብነት አንስተዋል፡፡
ከመነሻ እስከ መድረሻ ምንም የሚቆጣጠር የመንግሥት አካል አለመኖሩን ያስታወቁት ነዋሪዎቹ አሽከርካሪዎችና ረዳቶች ትርፍ እንዳይጫን የሚከላከሉትን በኃይል እንደሚቃወሙ ተናግረዋል፡፡ በሙሉ አቅማቸው ጭነው የሚጓዙት አውቶቡሶቹ ወደ ገንዳውኃ ከተማ ሲቃረቡ ለሚኒባስ ሾፌሮች ደውለው እንደሚጠሯቸውና ከቴክኒክና ሙያ ኮሌጁ አልፈው በመውጣት ከፊሉን ሰው እንዲቀበሏቸው በማድረግ ወደ ከተማ እንደሚገቡም ተናግረዋል፡፡
ነዋሪዎቹ እንዳሉት ከሕዝብ ትራንስፖርት ዘርፉ በተጨማሪ በሱዳን ድንበር አካባቢ የሚገቡና የሚወጡ በሞተር የሚጫኑ ሰዎች ስጋት ፈጥረውባቸዋል፡፡ ‘‘ሰውና ሸቀጥ በኮንትሮባንድ የሚያንቀሳቅሱ በርካታ ሞተረኞች አሉ’’ ያሉት ነዋሪዎቹ በአንድ ሞተር ሳይክል አራትና አምስት እየሆኑ በጫካ ውስጥ አቆራርጠው እንደሚገቡ አመልክተዋል፡፡
በተለይም በወረዳው ሽንፋ፣ መንዶካ፣ ቱመት እና ነፍስገበያ ቁጥር አራት አካባቢዎች ሕገወጥ እንቅስቃሴው የከፋ መሆኑን በመግለጽ መንግሥት አዋጁን እንዲያስከብር ጠይቀዋል፡፡ ጊዜው ወሳኝ የዘር ወቅት እንደሆነ ያስታወሱት ነዋሪዎቹ ‘‘በዚህ ወሳኝ ወቅት ወረርሽኙ ከገባ ሁሉ ነገራችን አደጋ ላይ ወድቃል፡፡ በበሽታም በርሃብም ልንጎዳ እንችላለን፡፡ መንግሥት ሕገ ወጥ ሞተረኞችንና በሕዝብ ትራስፖርት ዘርፍ የተሰማሩትን ሊቆጣጠርልን ይገባል’’ ብለዋል፡፡ ለአካባቢው ሚሊሻና ሌሎችም የፀጥታ ኃይሎች የትራንስፖርት እንቅስቃሴን እንዲቆጣጠሩ ኃላፊነት እንዲሰጥም ጠይቀዋል፡፡
የቋራ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ መብራቱ አዲሱ ግን የቁጥጥር ሥራው ተጠናክሮ መቀጠሉን በመግለጽ ቅሬታዎችን እንደግብዓት እንደሚወስዱ አስታውቀዋል፡፡ በሱዳን ጠረፍ አካባቢዎች ዘይትና መሰል ሸቀጦች በኮንትሮባንድ እንደሚገቡ የተናገሩት አቶ መብራቱ ፖሊስ፣ መከላከያና ሌሎችም የፀጥታ ኃይሎች ያሉበት ጥምር ኮሚቴ ሰፊ ክትትልና ቁጥጥር እያደረጉ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ነገር ግን ቦታው ሰፊ በመሆኑ ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር አልተቻለም፡፡ ‘‘ድንበሩ ከነፍስ ገበያ ቁጥር አንድ በአላጥሽ ፓርክ እስከ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ የሚደርስ ነው፡፡ እንቅስቃሴ በሚበዛባቸው አካባቢዎች ሁሉ ቁጥጥር እየተደረገ ነው፤ በቁጥጥር ሥር ያዋልናቸውም አሉ፡፡ ቁጥሩ የሚጨምርበትን አካባቢ ስንቆጣጠር በሌላ ቦታ የሚገቡም ይገባሉ፡፡ በብዛት የሚገባው ግን ዘይት ነው፤ የሰዎች እንቅስቃሴ አሁን ላይ ቀንሷል፤ ቀደም ብለው የገቡትንም ለይቶ ማቆያ አዘጋጅተናል’’ ብለዋል፡፡
የሕዝብ ማመላለሻ መኪኖች በግማሽ ቀንሰው እንዲጭኑ እየተደረገ መሆኑን ያስታወሱት አቶ መብራቱ በሻውራ በኩል ባሉ እንቅስቃሴዎች ችግር እንዳለ መረጃ እንደደረሳቸው አስታውቀዋል፡፡ ‘‘መናኸሪያ አካባቢ ቁጥጥር እየተደረገ ነው፤ የትራፊክ ፖሊሶች ቁጥር ውስን ነው፤ ነገር ግን በርካታ የሞተር እንቅስቃሴ መኖር የትራፊክ ፖሊሶችን ትኩረት ስቧል፡፡ አሁንም የሕዝቡን ጥቆማ መነሻ አድርገን የትራፊክ ፖሊሶች ቁጥጥር እንዲያደርጉ ይሠራል’’ ብለዋል፡፡
ኅብረተሰቡም በአዋጁ ከተቀመጣው ቁጥር በላይ ሆኖ ባለመሳፈር ራሱን ከኮሮና ወረርሽኝ እንዲጠብቅ ዋና አስተዳዳሪው አሳስበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- አብርሃም በዕውቀት
ፎቶ፡- ከፋይል
ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡