
ደብረ ታቦር: ግንቦት 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ)
ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ከነፋስ መውጫ እና ከላይ ጋይንት ወረዳ ነዋሪዎች ጋር እየተወያዩ ነው። በውይይቱ የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ፣ የአማራ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ አማረ ሰጤ፣ የአማራ ክልል ሚሊሻ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አስቻለ አላምሬ፣ የደቡብ ጎንደር ዞን አሥተዳደሪ ጥላሁን ደጀኔን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል። በውይይቱ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ ከሕዝብ ጋር በተደረጉ ውይይቶች በጋይንት ብዙ የተሻሻለ ነገር መኖሩን ገልጸዋል። ነገር ግን አኹንም ያልተፈቱ፣ የጠጠሩ እና መፈታት የሚገባቸው ጉዳዮች እንዳሉ አንስተዋል።
ከተከበረው ሕዝብ ጋር በመወያየት ችግሮችን መፍታት እንደሚገባም ገልጸዋል። ችግሮችን ለመፍታት መወያየት፣ መነጋገር እና አቋም መውሰድ ይጠበቅብናል ብለዋል። ክልሉ በገጠመው ችግር ምክንያት የክልሉ ሕዝብ ለጉስቁልና እና መከራ ተዳርጎ መቆየቱን ነው የገለጹት። ሕዝቡ በሰላም ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ እንዳይችል ኾኖ መቆየቱን ነው የተናገሩት። ባለፉት ጊዜያት በተሠራው ሥራ ክልሉ በአንጻራዊ ሰላም እንደሚገኝም ገልጸዋል። በጋይንት የተለየ ችግር መቆየቱን የተናገሩት ኀላፊው ይህ ድርጊት ለጋይንት ሕዝብ ሥነ ልቦና እንደማይመጥንም ተናግረዋል።
የጋይንት ሕዝብ በጀግንነት፣ በታላቅ ሥነ ልቦና እንጂ መኪና በማስቆም በዝርፊያ፣ በስርቆት አይታወቅም፣ ይሄን በአፋጣኝ ማስቆም ይጠበቅባችኋል፣ ይህ ለጋይንት ሥነ ልቦና አይመጥንም ነው ያሉት። የጋይንት ሕዝብ እንኳን ይሄን ችግር ሌላ የመፍታት አቅም እንዳለውም ተናግረዋል። የጋይንት ሕዝብ ታሪክ
የሚመሰክረው ችግር በገጠመው ጊዜ ፊት ቀድሞ የመፍትሔ አካል በመኾን ነው ብለዋል። በአካባቢው ያለውን ችግር ከመንግሥት ጋር በመኾን መፍታት እንደሚገባቸው ተናግረዋል። የታላቅ ሥነ ልቦና ባለቤት ሕዝብ ተራ ወንበዴን አደብ አስገዝቶ መፍታት አያቅተውም ነው ያሉት።
በጽንፈኛው እየተፈጸመ ያለው ድርጊት የሚያሳፍር እና አንገት የሚያስደፋ መኾኑን ነው የተናገሩት። “በአንድነት ተነስታችሁ ሰላማችሁን ማስከበር አለባችሁ” ያሉት ኀላፊው መንግሥት በሆደ ሰፊነት ለሰላም እንዲገቡ እየጠየቀ ነው፣ ለሰላም እንዲገቡ የበኩላችሁን ጠይቁ ብለዋል።
የሰላም አማራጭን በማይቀበለው ኀይል ላይ ግን የሕግ ማስከበር ሥራ እንደሚሠራ ተናግረዋል። የሕግ ማስከበር ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል። ሕዝቡ ለሕግ ማስከበር አቅም እንዲኾንም ጠይቀዋል። ሕዝቡ በአንድነት ተነስቶ ነጻነቱን ማረጋገጥ አለበት፣ የጋይንትን ሕዝብ ሥነ ልቦና ማስጠበቅ
አለበት፣ ጽንፈኞችን አጋልጦ መስጠት አለበት ነው ያሉት።
ሕዝቡ በአንድነት ከተነሳ ችግሩን መፍታት እንደሚችልም ተናግረዋል። አኹን ያለውን የሰላም መንገድ ካልተጠቀምንበት መከራ እና ችግሩ ይቀጥላል ነው ያሉት። ከችግር ለመውጣት በጋራ መሥራት እና ጽንፈኝነት በቃን ብሎ መነሳት ይገባል ብለዋል።
የእናንተን ገንዘብ እየዘረፉ የራሳቸውን ሀብት የሚያደርጁ ኀይሎችን መታገል አለባችሁ ነው ያሉት። በአንድነት ኾነን የጋይንትን ሕዝብ ሥነ ልቦና ማስከበር አለብን ብለዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን