ሰላም በይቅር ባይነት እና በአርቆ አሳቢነት የሚገኝ ነው።

6

ደብረ ታቦር: ግንቦት 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የክልል እና የዞን ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ከነፋስ መውጫ እና ከላይ ጋይንት ወረዳ ነዋሪዎች ጋር በሰላም ዙሪያ እየተወያዩ ነው።

በውይይቱ የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይረጋ ሲሳይ፣ የአማራ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ አማረ ሰጤ፣ የአማራ ክልል ሚሊሻ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አስቻለ አላምሬ፣ የደቡብ ጎንደር ዞን አሥተዳዳሪ ጥላሁን ደጀኔ እና ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።

በውይይቱ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የነፋስ መውጫ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ደጀን አከለ የገጠመንን ችግር ለመፍታት ማኀበረሰቡ ከመንግሥት ጎን ኾኖ ሢሠራ መቆየቱን ገልጸዋል።

የራስ ጋይንት ሕዝብ እንደ ጥንት አባቶቹ በየትኛውም ጊዜ የባንዳነት ሥራ የማይሠራ ከአመኑት የማይከዳ ታማኝ ሕዝብ ነው ብለዋል። በጨዋነት የሚኖር እና በሕግ የበላይነት የሚያምን እንደኾነም አስታውቀዋል።

የታላቅ ታሪክ ባለቤት የኾነው የዚህ ዘመን ትውልድም ሰላሙን በማጠናከር ልማቱን ማረጋገጥ አለበት ነው ያሉት።

ሰላም ለሰው ልጅ ልክ እንደ እስትንፋስ ሁሉ አስፈላጊ ነው ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው የሰላምን ትርጉምና ዋጋ ከፍ አድርገን በመመልከት ለሰላም በጋራ መሥራት አለብን ብለዋል።

ልዩነትን በመቻቻል፣ በውይይት እና በሰላማዊ መንገድ ባለመፍታት በተደረጉት በርካታ ግጭቶች አኹን ድረስ ስብራታቸው ያልጠገነ እና በርካታ ውስብስብ ሰባዓዊ ጥፋቶች ደርሰዋል ነው ያሉት።

በክልሉ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር በርካታ ጉዳት መድረሱንም ተናግረዋል። ችግሮቻችን በውይይት እና በሰላም መፍታት ይገባልም ብለዋል።

የደቡብ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ጥላሁን ደጀኔ “ሰላም በይቅር ባይነት እና በአርቆ አሳቢነት የሚገኝ ነው” ብለዋል። ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ መምክር እና መወያየት መፍትሔ መኾኑንም ገልጸዋል። ባለፉት ጊዜያት በተፈጠሩ የጸጥታ ችግሮች በርካታ ጉዳቶች ደርሰዋል ነው ያሉት።

ጽንፈኝነት ለሕዝብ እና ለሀገር የማይጠቅም መኾኑንም ተናግረዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleበክልል አቀፍ ደረጃ በሚሰጡ ፈተናዎች የተሻለ ውጤት እንዲመዘገብ ምን ዝግጅት ተደርጓል?
Next article“በአንድነት ተነስታችሁ ሰላማችሁን ማስከበር አለባችሁ” አቶ ይርጋ ሲሳይ