
ባሕር ዳር: ግንቦት 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የፈተና እና ምዘና የትምህርት ሥርዓት ጥንካሬዎች እና ድክመቶችን ከመለየት ባለፈ የሀገሪቱን የወደፊት አቅጣጫ መወሰን የሚችል ብቃት ያለው የሰው ኀይል ለማፍራት ትልቅ ፋይዳ አለው።
በተያዘው በጀት ዓመት በአማራ ክልል የ8ኛ ክፍል ፈተና ከሰኔ 3/2017 ዓ.ም እስከ ሰኔ 4/2017 ዓ.ም፣ የ6ኛ ክፍል ደግሞ ከሰኔ 5/2017 ዓ.ም እስከ ሰኔ 6/2017 ዓ.ም ይሠጣል። የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ መረጃ እንደሚያሳየው 51 ሺህ 377 ተማሪዎች ደግሞ ፈተናውን ይወስዳሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ለመኾኑ ተፈታኝ ተማሪዎች ዝግጅታቸው ምን ይመስላል? በደቡብ ወሎ ዞን ቃሉ ወረዳ የጃሮታ አንደኛ እና መካከለኛ ትምህርት ቤት የ8ኛ ክፍል ተማሪ አባስ አብዱ ተሞክሮውን አጋርቶናል። ተማሪው ክፍል ውስጥ በመምህራን የሚሰጡ ትምህርቶችን በትኩረት እንደሚከታተል ገልጿል።
ወደ ቤት ከተመለሰ በኋላ ደግሞ የተማረውን ትምህርት ያነባል፤ በአብዛኛው የማታ ጊዜውን ለንባብ ይጠቀማል። በቀን በአማካይ እስከ ሦስት ሰዓት ያለውን ጊዜ በንባብ እንደሚያሳልፍም ነው የተናገሩት። ቤተ መጽሐፍት ውስጥ ማጣቀሻ መጽሐፍት ላይ ትኩረት እንደሚያደርግም ነግሮናል።
በበጀት ዓመቱ በመምህራን የተሠጡ ማጠናከሪያ ትምህርቶች፣ የብቃት ፈተናዎች፣ የጥያቄ እና መልስ ውድድሮች የተማሪዎችን የማብቃት አቅም ይበልጥ የሚያሳድጉ መኾናቸውን ተማሪ አባስ ገልጿል። አኹን ላይም የንብብ ጊዜውን በማሳደግ ዋና ዋና ርዕሰ ጉዳዮች ላይ በማተኮር እያነበበ ይገኛል። የተለያዩ ጥያቄዎችንም በመሥራት ራሱን እያዘጋጀ መኾኑን ነው የገለጸው።
በዚህ ዓመት ከ90 በመቶ በላይ ውጤት ለማስመዝገብ ቅድመ ዝግጅት ማድረጉን ነው የገለጸው። በ2017 የትምህርት ዘመን ትምህርት ቤቱ የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግብ የተለያዩ ሥልቶችን በመቀየስ እየተሠራ መኾኑን በቃሉ ወረዳ የጃሮታ አንደኛ እና መካከለኛ ትምህርት ቤት ርእሰ መምህር ሰዒድ እሸቱ ተናግረዋል።
ርእሰ መምህሩ የ2017 የትምህርት ዘመን ከተጀመረ ጀምሮ ተማሪዎችን የማብቃት እና የማዘጋጀት ሥራ ሲሠራ ቆይቷል ነው ያሉት። የተማሪዎችን ውጤታማነት ለማሳደግ ከተሠሩ ሥራዎች ውስጥ ከዚህ በፊት ተሠርተው የፈረሱ የመማሪያ ክፍሎችን በመገንባት ተማሪዎች የመደበኛ ትምህርት እንዲጀምሩ ተደርጓል ብለዋል።
ከመደበኛው የመማር ማስተማሩ ባለፈ በዋነኝነት የማጠናከሪያ ትምህርት ላይ ትኩረት ተደርጓል ነው ያሉት። ተማሪዎች በቡድን እንዲያጠኑ፣ ቤተ መጽሐፍትን በማጣቀሻ መጽሐፍት ማጠናከር እና አብዛኛውን ጊዜ ክፍት በማድረግ ተማሪዎች እንዲያነቡ ተደርጓል ብለዋል። ጎበዝ ተማሪዎች ክፍል ውስጥ እና ከክፍል ውጭ ሌሎች ተማሪዎችን እንዲያግዙ፣ የጥያቄ እና መልስ ውድድሮች ከትምህርት ቤት ባለፈ በጉድኝት ጭምር በማካሄድ ተማሪዎችን የማዘጋጀት ሥራ ሲሠራ መቆየቱን ነው የገለጹት።
በመደበኛ እና በማጠናከሪያነት ከተማሩት ትምህርት በወር አንድ ጊዜ የብቃት ፈተና እንዲወስዱ ተደርጓል ነው ያሉት። ከዚህ በፊት ተማሪዎች በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት የተፈተኗቸውን ወርክ ሽቶች እንዲሠሩ መደረጉንም ገልጸዋል። የደቡብ ወሎ ዞን ትምህርት መምሪያ ሥርዓተ ትምህርት ቡድን መሪ ሰዒድ ሙሐመድ በዞኑ የሚገኙ ትምህርት ቤቶችን ውጤታማነት ለማረጋገጥ ከመደበኛ መማር ማስተማሩ ባለፈ ቅዳሜ እና አሑድ እንድኹም የተቃራኒ ፈረቃን በመጠቀም በተመረጡ ርዕሶች እና ተማሪዎች ባልተገነዘቧቸው ርዕሶች ላይ የማጠናከሪያ ትምህርት ሲሰጥ ቆይቷል ብለዋል።
ያለፉ ዓመታት ጥያቄዎችን በማሰባሰብ ተማሪዎች እንዲሠሩ፣ የመለማመጃ ጥያቄዎችን በማዘጋጀት የማገዝ ሥራ እየተሠራ ይገኛል ነው ያሉት። በሥነ ልቦና እንዲዘጋጁ የምክር አገልግሎት በየጊዜው አየተሠጠ ነውም ብለዋል። በቀጣይ የሚሰጠውን ፈተና ተማሪዎች በተረጋጋ መንገድ ወስደው የተሻለ ውጤት እንዲያመጡ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጠይቀዋል።
በ2017 የትምህርት ዘመን በዞኑ በ435 የ8ኛ ክፍል ትምህርት ቤቶች 23 ሺህ 735 ተማሪዎች፣ በ617 የ6ኛ ክፍል ትምህርት ቤቶች ደግሞ 23 ሺህ 74 ተማሪዎች ይፈተናሉ ብለዋል።
ዘጋቢ: ዳግማዊ ተሠራ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን