
ባሕር ዳር: ግንቦት 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ዲጅታል መታወቂያ ወይም ፍይዳ በአዋጅ ቁጥር 1284/2015 ላይ በሕግ እውቅና የተሠጠው የማንነት መገለጫ ወይም መለያ ነው። ፋይዳ የኢትዮጵያ ዲጂታል መታወቂያ ሲኾን ቴክኖሎጂን በመጠቀም የነዋሪዎችን የተመጠነ የባዮሜትሪክ እና ዲሞግራፊክ መረጃ በመሠብሠብ አንድን ሰው ልዩ በኾነ ኹኔታ መለየት የሚያስችል ሥርዓት ነው ማለት ይቻላል።
የፋይዳ ቁጥር በብሔራዊ መታወቂያ መርሐግብር የተቀመጠውን ቅድመ ኹኔታ ለሚያሟሉ ነዋሪዎች የሚሰጥ ባለ 12 ወይም ባለ 16 አሐዝ ልዩ መለያ ቁጥር ተሰጥቶት የሚያገለግል የግለሰቦች የማንነት መገለጫ ወይም መለያ ነው ሲል አዋጁ በግልጽ አስቀምጦት ይገኛል። ፍይዳ በሀገሩቱ ተግባራዊ መኾንም በቴክኖሎጅው ዓለም ከዘመኑ ጋር ለመራመድ ጥቅሙ የጎላ ነው እየተባለለት ነው።
በብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም የባለድርሻ አካላት ዳይሬክተር ሳሚናስ ሰይፉ ፋይዳ መታወቂያ ግለሰቦችን ወይም ነዋሪዎችን በልዩነት ለማወቅ የሚረዳ የማንነት መገለጫ ወይም መታወቂያ ነው ብለዋል። ከሕግ አንጻር የኢትዮጵያ ዲጅታል መታወቂያ ከለላ የተሰጠው ነው ብለዋል። ፋይዳን በሁሉም ማኅበረሰብ ዘንድ ለማዳረስ መረጃዎች እንዴት እንደሚሠበሠቡ፤ እንዴት ማስቀመጥ እንደሚቻል፤ እንዴት መጠቀም እንዳለብ እና እንዴት ማጋራት እንደሚቻል በአዋጁ በግልጽ የተቀመጠ ስለመኾኑም ገልጸዋል።
ብሔራዊ መታወቂያን ማውጣት አስገዳጅ አይደለም ይላሉ አቶ ሳሚነስ። ይኹን እንጅ ከዘመኑ መለወጥ እና ከዲጅታል ቴክኖሎጅ አንጻር ተቋማት የሚያስገድዱበት ኹኔታ እየተፈጠረ ነው ብለዋል። ማንኛውንም አገልግሎት ለማግኘት ተቋማት የሚጠቀሙት ለደኅንነት ሲባል ዲጅታል መታወቂያን አዋጁ አለማስገደድ መፍትሔ አይኾንም ነው ያሉት።
አዋጁ ተጠያቂነትን እና ኀላፊነትን የሚወስን አዋጅ እንደኾነም ተናግረዋል። ለምሳሌ የዲጅታል መታወቂያ ባለቤት ለመኾን የጣት ሻራ፣ የዐይን አሻራ እና ሌሎች መስፈርቶችን ማሟላት ከተቻለ ብቻ እንደኾነም ወስኖ ያስቀመጠ ነው ብለዋል። የትኞቹ የኅብረተሰብ ክፍሎች ይመዘገባሉ የሚለውንም ያስቀመጠ እንደኾነ ነው የተናገሩት። ከዚህ አንጻር ሁሉም ኢትዮጵያዊ የፋይዳ መታወቂያ ተመዝግቦ ባለቤት መኾን እንደሚችልም ተናግረዋል።
የውጭ ሀገር ዜጎች እና ስደተኞች መታወቂያውን እንዴት መውሰድ እንደሚችሉም ተናግረዋል። የአዋጅ ቁጥር 1284/2015 ዓ.ም መደንገግ ዲጅታል መታወቂያው በሀገሪቱ ተግባራዊ እንዲኾን እና አሠራሩ ነፍስ እንዲዘራበት ያደረገ ነው ብለዋል። አዋጁ የትኛውም ተቋም እና ግለሰብ የሚሠበሥበውን መረጃ እንዴት እንደሚያስቀምጥ እና እንዴት እንደሚያጋራም ግልጽ አድርጓል ብለዋል።
አዋጅ ቁጥር 1284/2015 ዓ.ም ከዲጅታል መታወቂያ አንጻር መብት እና ግዴታንም ለይቶ አስቀምጧል ብለዋል አቶ ሳሚናስ። ፋይዳን መመዝገብ መብት እንጅ ግዴታ አይደለም በሚል ይገልጻል ነው ያሉት። የመረጃ አስቀማጩ ተቋም የወጣውን የማንነት መገለጫ መታወቂያ በታማኝነት የማስቀመጥ ግዴታ እንዳለበት በግልጽ ተቀምጧል ብለዋል።
ዲጂታል መታወቂያ ለማግኘት ዘር፣ ጾታ፣ ሃይማኖት ያለየ እና አግላይ እንዳልኾነ በአዋጁ የተቀመጠ እንደኾነ ነው የተናገሩት። የባዮሎጂካል አሻራ መስጠት የሚችል ሁሉ መታወቂያውን ማግኘት እንደሚችልም የተቀመጠ ነው ብለዋል። አኹን ካለን የቴክኖሎጅ አቅርቦት አንጻር ከአምስት ዓመት ጀምረው አሻራ መስጠት አንደሚቻልም ነው የገለጹት።
ይህ የኾነው ግን ከአምስት ዓመት በታች ያሉ ሕጻናት የጣት አሻራቸው ስለማይበለጽግ እንደኾነም ነው የተናገሩት። ቴክኖሎጅዎች በመጠቁ ቁጥር ግን ሊሻሻል ይችል ይኾናል ብለዋል። ከዚህ በተጨማሪ ማንኛውም የፍይዳ መታወቂያን ለሚፈልግ ሁሉ ምዝገባው በነጻ እንደኾነ ይገልጻል ነው ያሉት። የፋይዳ መታወቂያው ባለ 12 እና ባለ 16 ዲጅት ቁጥር ነው። ለዚያ ምንም አይነት ገንዘብ አያስወጣም ነገር ግን ቁጥሩን ለማውጣት የሚያገለግለውን ካርድ ለመያዝ ግን ዜጎች ለካርዱ ወጭ ሊጠየቁ ይችሉ ይኾናል ነው ያሉት።
ስለዚህ ወጭ ካስወጣ እንኳ መታወቂያው ሳይኾን የመታወቂያው ካርድ ነው ይላሉ። የግለሰቡ መሠረታዊ መታወቂያው ቁጥሩ እንደኾነም አመላክተዋል። ሰዎች ፍይዳን የመመዝገብም ኾነ ያለመመዝገብ መብት እንዳላቸው በአዋጁ ተመላክቷል። ነገር ግን ተቋማት በአሠራር ላይ እንደ ሥራ ባህሪያቸው እና ፍላጎታቸው አስገዳጅ የማድረግ ሥልጣን ተሰጥቷቸዋል ብለዋል።
ተቋማት ሲባልም የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ሳይኾን ሌሎች ማንኛውም ተቋማት ማለት እንደኾነም አብራርተዋል። ለአብነት ብለው ያነሱት አቶ ሳሚናስ የቲን ቁጥር ለማውጣት ፋይዳ መታወቂያ የግድ ሊያደርጉት ይችላሉ ነው ያሉት።
ስለዚህ ዜጎች የፋይዳ መታወቂያን ምንም ለድርድር የማይገባ መሠረታዊ ነገር መኾኑን መገንዘብ ይኖርባቸዋል ብለዋል።
ስለኾነም ይላሉ አቶ ሳሚናስ ፋይዳ ዜጎች መብታቸውን ተጠቅመው ሊገለገሉበት የሚገባ መሠረታዊ ነገር ነው።
ዘጋቢ: ሰለሞን አንዳርጌ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
