
ባሕር ዳር: ግንቦት 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ሰኔ ግም ሲል የሰማይ ደመናው ውኃ ሲያዝል አርሶ አደር ደስታው ከፍ ያለ ነው፡፡ የተሰቀሉ እርፍ እና ሞፈሩን አዋዶ በሬውን ጠምዶ ማረስ ማረስ ይጀምራል፡፡ አርሶ አደሩ በሬውን ጠምዶ እንዲህ ይላል፡- ያረሰማ ጎበዝ እርፍ የነቀነቀ ወፍጮው እንዳጎራ መስከረም ዘለቀ።
ይህ ግጥም በአርሶ አደሩ የሚያምር ቅላጼ ታግዞ ግባ ወይኖ እና ኮልባ እያለ በሬዎቹን እያባበለ ሰማዩ ያዘለውን ዝናብ ባረሰረሰው መሬት ላይ እየገመሰ እርሻውን ያርስ ዘንድ የግድ ይለዋል፡፡ ይህም ለነገ ሕይዎቱ መሳካት የግድ ይላል እና መሬቱን ጠንክሮ ያርሳል፡፡ አርሶ አደር አማኑኤል አሰፋ እርፍ እና ሞፈራቸውን አዋድደው ወይኖን እና ኮልባን ጠምደው የሚያርሱ ጎበዝ የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን አርሶ አደር ናቸው፡፡
አርሶ አደሩ ከዚህ በፊት የመንግሥት ሠራተኝነቱን የሞከሩ ቢኾንም ማን እንደ ገበሬ ከራስ የተሻገረ የሀገር ተስፋ እና ማገር ብለው ወደ እርሻቸው ተመልሰዋል፡፡ አርሶ አደር አማኑኤል አኹን በተሰማሩበት ግብርና ውጤታማ መኾናቸውንም በኩራት ነው የሚናገሩት፡፡ እርሻን ውጤታማ የሚያደርገው ደጋግሞ ማረስ እንደኾነ የሚናገሩት አርሶ አደሩ ለዚህም ደጋግመው እንደሚያርሱ እና በጊዜውም እንደሚያርሱ ነው ለአሚኮ የተናገሩት፡፡
ለ2017/2018 የመኸር ምርት ዘመን የእርሻ መሬታቸውን ለማረስ ዝግጅት ላይ መኾናቸውን የሚናገሩት አርሶ አደር አማኑኤል አሰፋ መሬታቸውን ሰሊጥ፣ ማሽላ፣ ማሾ እና ሱፍ በስፋት ለመዝራት ደጋግመው እንደሚያርሱ ነግረውናል፡፡ አርሶ አደር አማኑኤል አሰፋ በዚህ ዓመት ደጋግመው በማረስ፣ የተሻሻሉ ቴክኖሎጅዎችን፣ የተፈጥሮ ማዳበሪያ እና ምርጥ ዘሮችን በመጠቀም ከ1ሺህ 400 ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት በማሰብ ወደ ሥራ እንደገቡ ነው ያብራሩት፡፡
የተሰማሩበት የእርሻ ሥራ ኑሯቸውን እንደለወጠላቸው የተናገሩት አርሶ አደሩ ለዚህም የሰላም ኹኔታው የተሻለ መኾኑ ከሌሎች አካባቢዎች በነጻነት ለመሥራት እንዳገዛቸው ነው ያብራሩት፡፡ ሰላም የሁሉም ነገር መሠረት ነው ያሉት አርሶ አደሩ ከራስ አልፎ ለወገን ለመትረፍ ሰላምን ማስጠበቅ ይገባል ነው ያሉት፡፡
አኹን ላይ አካባቢው ሰላም ቢኾንም ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሶ ለምርታማነቱ አስፈላጊ የኾኑ ግብአቶችን ለማቅረብ መንገድ ላይ የሚገጥሙ ችግሮች ስጋት መኾናቸውን እና ይህም የእርሻ ሥራቸውን እየጎዳ በመኾኑ ሁሉም ለሰላም እንዲረባረብ ነው የጠየቁት፡፡ ትርፍ አምራቹ የምሥራቅ ጎጅም ዞን ሁለት እጁ እነሴ ወረዳ አርሶ አደር በላይ ሽባባው የሰላም ኹኔታው ከባለሙያዎች ጋር እየመከሩ በተሻለ መንገድ አርሰው የተሻለ ምርት እንዳያመርቱ እንቅፋት ፈጥሮ መቆየቱን ነው የሚናገሩት፡፡
ቀያቸው ሰላም በነበረበት ጊዜ ከግብርና ባለሙያ ጋር መክረው እና ቴክኖሎጅዎችን ተጠቅመው ከራሳቸው አልፈው ለሌላው ይተርፉ እንደነበር አስረድተዋል፡፡ በርግጥ አኹን ላይ እንዳለፈው ክረምት የሰላሙ ኹኔታ አስጊ ባይኾንም የተሻለ ሠርተው ከጤፍ እና ከስንዴ ምርት ብቻ እስከ 100 ኩንታል ምርት ከዚህ በፊት እንደሚያገኙት በዚህ ዓመትም ለማግኘት እየሠሩ ስለመኾናቸው አስረድተዋል፡፡ ሰላምን ማስጠበቅ ላይ ግን ሁሉም ርብርብ እንዲያደርግ ነው ያሳሰቡት፡፡
የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ግብርና መምሪያ ኀላፊ አወቀ መብራቱ ለ2017/2018 ዓ.ም የመኸር እርሻ ልማት 561 ሺህ ሄክታር መሬት በተለያዩ የሰብል አይነቶች ለመሸፈን የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል፡፡ በዚህም ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ሰሊጥ፣ አኩሪ አተር፣ ማሾ እና ለምግብነት የሚያገለግሉ የተለያዩ ሰብሎች ይለማሉ ነው ያሉት፡፡
ከሚለማው መሬት 13 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃልም ብለዋል፡፡ ይህንን የምርት መጠን ውጤታማ ለማድረግ ከዞን ጀምሮ እስከ ቀበሌ ያሉ ባለሙያዎች እና አርሶ አደሮች ሥልጠና ተሰጥተዋል ነው ያሉ፡፡ ምርቱንም ለማግኘት እርሻ ላይ በሚገባው ደረጃ እንዲታረስ ለማድረግ እየሠሩ ስለመኾኑ ነው የጠቆሙት፡፡ በአካባቢው ያለው የሰላም ሁኔታም ባለሙያው አርሶ አደሩን ለመደገፍ እንዳስቻለው ተናግረዋል፡፡ የሚጠብቁትን የምርት መጠን እንደሚያገኙም ተስፋ ማድረጋቸውን ነው ለአሚኮ የተናገሩት፡፡
የምሥራቅ ጎጃም ዞን ግብርና መምሪያ ኀላፊ አበበ መኮነን በበኩላቸው በዞኑ በ2017/2018 በጀት ዓመት የምርት ዘመን 642 ሺህ 585 ሄክታር መሬት እንደሚያለሙ ተናግረዋል፡፡ ከዚህም 25 ነጥብ 1 ሚሊዮን ምርት ይጠበቃል ነው ያሉ፡፡ ቀደም ሲል የሰላሙ ሁኔታ በዞኑ አስቸጋሪ ስለነበር ቀበሌ ድረስ ወርደው ለመደገፍ ይቸገሩ እንደነበር ተናግረዋል፡፡
በዚህ ዓመት ግን የተሻለ ሰላም በመኖሩ በዞኑ ከታቀደው እስከአሁን ባለው 81 በመቶ የሚኾነው መሬት እንደየ ሰብሉ አይነት እና ባህሪ ከአንደኛ እስከ አራተኛ እርሻ የማረስ እና የማለስለስ ሥራ መሠራቱን ተናግረዋል፡፡ ከዚህ ውስጥ ወደ 2ሺህ 652 ሄክታር የሚኾነውን በትራክተር ለማረስ ጥረት መደረጉንም ነው ኀላፊው የተናገሩ፡፡ አጠቃላይ ከሚለማው ውስጥ 435ሺህ 948 ሄክታር መሬት በክላስተር በተመረጡ ዋና ዋና ሰብሎች ጤፍ፣ ስንዴ፣ በቆሎ፣ ማሽላ፣ ቦሎቄ እና የቢራ ገብስ ይሸፈናል ነው ያሉት፡፡
በአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የሰብል ልማት እና ጥበቃ ዳይሬክተር ማንደፍሮ አስላከ (ዶ.ር) እንደተናገሩት በ2017/2018 በጀት ዓመት የመኸር እርሻ ልማት 5 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ለማልማት በታቀዱን አስገንዝበዋል፡፡ ለዚህም የእርሻ ሥራው በሚገባ እንዲሠራ አስፈላጊው ድጋፍ ለአርሶ አደሮች እንደሚደረግ ገልጸው ከዚህም ሥራ 187 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይጠበቃል ብለዋል፡፡
የሚጠበቀው ምርትም ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ17 ሚሊዮን ኩንታል ብልጫ እንደሚኖረው አስገንዝበዋል፡፡ እስካኹን ባለው 3 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሄክታር መሬት መታረሱን የተናገሩት ዳይሬክተሩ ከ100 ሄክታር መሬት በላይ ቀድመው በሚዘሩ ሰብሎች በዘር መሸፈኑንም ነው የተናገሩት፡፡
ዶክተር ማንደፍሮ አስላከ እንዳሉን ወደ እርሻ ከመገባቱ በፊት ከክልል እስከ ቀበሌ ያሉ ባለሙያዎችን እና አርሶ አደሮችን በተለያዩ ቦታዎች የተሻሻሉ አሠራሮችን ተግባራዊ አድርገው የተሻለ ምርት ለማግኘት ሥልጠና ተሰጥቷል፡፡ በዚህም አርሶ አደሩ በሠለጠነበት አግባብ እና በባለሙያው ምክረ ሀሳብ በመታገዝ ምርጥ ዘርን እና ማዳበሪያን መጠቀም እንዲችሉ ብሎም ከባሕላዊ እርሻ ተላቅቀው ዘመናዊ እርሻን ተከትለው ምርታማነትን ማሳደግ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ሰናይት በየነ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን