
ኅብረተሰቡ የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል ከዚህ ቀደሙ በተሻለ መጠንቀቅ እንዳለበት ጤና ቢሮው አሳስቧል፡፡
ባሕርዳር፡ ግንቦት 17/2012 ዓ.ም (አብመድ) የአማራ ክልል ጤና ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ዋለ በላይነህ ለአብመድ አንደተናገሩት በክልሉ የትናንትና የዛሬን የምርመራ ቁጥሮች ሳይጨምር ለ930 ሰዎች ምርምራ ተደርጎ ነው 27 ሰዎች ቫይረሱ የተገኘባቸው፡፡ እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ በሕክምና ላይ ከሚገኙት ሕሙማን መካከል አንድም በጽኑ ሕሙማን መታከሚያ ውስጥ የለም፤ ሁሉም በጥሩ ጤንነት ላይ ይገኛሉ፡፡
በክልሉ አብዛኛውን ቁጥር የሚይዙት በምዕራብ ጎንደር ዞን ሱዳን ጠረፍ በኩል የሚገቡ ዜጎች መሆናቸውንም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡
‘‘ኅብረተሰቡ የኮሮና ቫይረስን ለመካከል እና ለመቆጣጠር ያለው ትኩረት ቀንሷል’’ ያሉት ዳይሬክተሩ አሁን ላይ የጉዞ ታሪክ የሌላቸው፣ በቫይረሱ ከተያዙት ጋር ንክኪ ስለመኖራቸው ባልተረጋገጡትም የኮሮናቫይረስ እየተገኘባቸው በመሆኑ ኅብረተሰቡ የበለጠ ጥንቃቄ በማድረግ ራሱንና ቤተሰቡን ከአስከፊው ወረርሽኝ መጠበቅ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
ወረርሽኙ አስከፊ ጉዳት እንዳያደርስ የጤና ተቋማትና መንግሥት በትኩረት መሥራት፣ የሕግ ማስከበር ሥራው መጠናከርና ማኅበረሰቡም የጥንቃቄ መመሪያዎችን መተግበር እንደሚገባ ነው ያስገነዘቡት፡፡
የክልሉ ጤና ቢሮም ከዚህ ቀደም የነበረውን እቅድ በመከለስ ወደ ሥራ እንደገባና በክልሉ ለቫይረሱ ተጋላጭነታቸው ከፍ ያሉ 75 ወረዳዎችም ተለይተው በትኩረት እየተሠራ መሆኑን አቶ ዋለ ተናግረዋል፡፡
በአማራ ክልል አምስት የኮሮናቫይረስ መመርመሪያ ማዕከላት ወደ ሥራ ገብተዋል፡፡ እነዚህም የክልሉ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት (ባሕርዳር እና ደሴ)፣ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል፣ ወሎ ዩኒቨርሲቲ እና ደብረ ብርሃን ሪፈራል ሆስፒታል ናቸው፡፡ በቅርቡ ደግሞ በጥበበ ግዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታልና በእንጅባራ ከተማ ምርመራ ለመጀመር እየተሠራ እንደሆነ ታውቋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡