“ሀገር የምትቀጥለው ሳይሰስቱ ደም እና አጥንታቸውን በሚገብሩ ውድ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ነው” ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)

21

ወልድያ: ግንቦት 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ከፍተኛ መሪዎች በሰሜን ወሎ ዞን ሀብሩ ወረዳ በመገኘት የመከላከያ ሠራዊት አባላትን አበረታተዋል።

በጉብኝቱ የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)፣ የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኀላፊ ፍሰሐ ደሳለኝ፣ የአማራ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኀላፊ መንገሻ ፈንታውን (ዶ.ር) ጨምሮ የተለያዩ መሪዎች ተገኝተዋል።

“በክልሉ ከፍተኛ መሪዎች በመጎብኘታችን እጅግ ደስተኛ ነን” ያሉት በሀገር መከላከያ ሠራዊት የ802 ኮር አዛዥ ኮሎኔል ቢራራ ሙልየ ወታደሮቹ በግዳጅ ላይ እያሉ ብቁ የሚያረጋቸውን የክህሎት ሥልጠና በራሳቸው በወታደሮች እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።

በማሠልጠኛ ቦታው የክልሉ የጸጥታ ኃይሎች በመምጣት የአቅም ማጎልበት ልምምድ እንደሚወስዱበትም ገልጸዋል።

“ሀገር የምትቀጥለው ሳይሰስቱ ደም እና አጥንታቸውን በሚገብሩ ውድ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ነው” ያሉት የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) ክልሉን ለማረጋጋት ለምትከፍሉት መስዋትነት በክልሉ እና በመላው ኢትዮጵያውያን ስም ምሥጋና ይገባችኋል ብለዋል።

መከላከያ ሠራዊቱ በሚፈልገው በማንኛውም ተግባር ላይ የክልሉ ሕዝብ ግንባር ቀደም እንደሚኾን ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ ተናግረዋል። “ይህንን የምናደርገው በጎ ለመባል ሳይኾን ግዴታችን ስለኾነ ነው” ብለዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous article“የፈጠራ ምንጮች አነስተኛ የሚመስሉ አስገራሚ ሀሳቦች ናቸው” ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር)
Next articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በገጠር ሞዴል የአርሶ አደሮች መኖሪያ መንደር ሥራን አስጀመሩ።