“የፈጠራ ምንጮች አነስተኛ የሚመስሉ አስገራሚ ሀሳቦች ናቸው” ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር)

7

ባሕር ዳር: ግንቦት 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የተማሪዎች እና መምህራን ሳይንሳዊ የፈጠራ ሥራዎች ላይ አውደ ርዕይ አካሂዷል፡፡ በአውደ ርዕዩ የከተማ አሥተዳደሮችን ጨምሮ ከሁሉም የክልሉ ዞኖች የተውጣጡ መምህራን እና ተማሪዎች ተሳትፈዋል፡፡ የፈጠራ ውድድር እና ሽልማትም ተደርጓል፡፡

ሳምራዊት እና ጓደኞቿ በባሕር ዳር ከተማ የኤስ.ኦ.ኤስ ሀርማን ግማይነር ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል ተማሪ ናቸው፡፡ በአንደኛነት የተሸለሙበት ያበለጸጉት ፊቸር ፎከስ የተባለ ዌብሳይት ነው፡፡ ዌብሳይቱ ለ11ኛ ክፍል ተማሪዎች የሚያገለግሉ መጻሐፍት፣ ጥያቄዎች እና ተንቀሳቃሽ ምስሎች የተጫኑበት ነው፡፡ ወደፊትም ይስፋፋል ብለዋል፡፡

በቀጣይ ዌብሳይቱ ያለ በይነ መረብ ትስስር (Offline) ማግኘት እንዲቻል አስበው እየሠሩም ነው፡፡ እነ ሳምራዊት በየችሎታቸው በመተጋገዝ መሥራታቸውን ተናግረዋል፡፡ ሌሎች ተማሪዎችም ጊዜያቸውን በአግባቡ ተጥቅመው በመሥራት ውጤታማ እንዲኾኑ መክረዋል፡፡

በዋግ ኽምራ ዞን ሰቆጣ ከተማ አሥተዳደር የዋግ ስዩም አድማሱ ወሰን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት 12ኛ ክፍል ተማሪ ምስጋናው ደርበው ተወንጫፊ ሮኬት ሠርቶ ሁለተኛ ደረጃን አግኝቷል፡፡ ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ በፈጠራ ላይ አተኩሮ እንደሚሠራ፣ በዚህም ሩሲያ ሂዶ ልምድ መቅሰሙን ተናግሯል፡፡
ሮኬቱ አራት ደረጃዎችን ማለፉን እና አኹን ላይ 15 ኪሎ ሜትር ርቀት ውጤታማ ርቀት መወንጨፉን ተናግሯል፡፡

ዓላማው ኢትዮጵያን በስፔስ ሳይንስ ማሳደግ መኾኑንም ገልጿል፡፡ ማኅበረሰቡም ለፈጠራ ሥራ በሀሳብ እና በገንዘብ ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቋል፡፡ በደቡብ ጎንደር ዞን ታች ጋይንት ወረዳ የዶክተር አንባቸው መኮንን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የቴክኒክ ዲሮዊንግ መምህር አሥራቴ ታደሰ ደግሞ በድር እና ማግ ማቅለሚያ፣ ማጠንጠኛ እና መፍተያ ማሽን ፈጠራ እንዲኹም በምርጥ ወንድ የፈጠራ መምህር በአንደኛነት ተሸልሟል፡፡

የተለያዩ የፈጠራ ፕሮጀክቶቹን ወደ ተግባር ቀይሮ ማኅበረሰቡን የሚጠቅሙ ማድረግ እና ተማሪዎችንም ተመርቀው ሥራ ፈጣሪ እንዲኾኑ ስለማድረግ እያሰበ መኾኑን ተናግሯል፡፡ እስካኹን አራት ጊዜ ተወዳድሮ ለሁለተኛ ጊዜ ተሸልሟል፡፡ በሀሳብ ደረጃ ከሚያግዙ ጥቂት አደረጃጀቶች በስተቀር ድጋፍ የሚያደርግ አለመኖሩንም ጠቅሷል፡፡ የክልሉ መንግሥት ለዘርፉ ትኩረት በመስጠት ሥራውን የሚደግፍ እና የሚከታተል ተቋም እና አሠራር እስከ ወረዳ ድረስ እንዲያበጅ አሳስቧል፡፡

ሌላኛዋ በፈጠራ እና በምርጥ ሴት ፈጣሪ የተሸለመችው በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ከምዕራብ ደንቢያ ወረዳ መስቀለ ክርስቶስ ትምህርት ቤት የባዮሎጂ መምህር አሰፉ መሌ ናት፡፡ ተወዳድራ የተሸለመችበት ከተፈጥሮ ንጥረ ነገር የሠራችው የጸጉር ቅባት ቢኾንም ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ ሽቶ፣ ሻምፖ፣ ፈሳሽ ሳሙና፣ ሻማ፣ እስክርቢቶ፣ ማርከር፣ ጸረ ተባይ መድኃኒት እና ባዮ ጋዝ መፍጠሯን ገልጻለች፡፡

ከማኅበረሰቡ እና ከተቋማት ማበረታቻ እንደምታገኝ የተናገረችው መምህር አሰፉ እሷም በበኩሏ ተማሪዎቿን እያስተማረች እንደኾነ ተናግራለች፡፡ ሙሉ ጊዜዋን በፈጠራ ሥራ ለማዋል የሚደግፋት እንደምትፈልግም ተናግራለች፡፡ የአማራ ክልል ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ቢሮ ኀላፊ አቤል ፈለቀ በሳይንሳዊ ፈጠራ ላይ ማኅበራዊ መሠረት ያለው ሥራ መጀመሩን ገልጸዋል፡፡ ለተማሪዎች እና መምህራን የፈጠራ ሀሳብን ማፍለቅ፣ ማጎልበት እና መሥራት አስፈላጊውን ሁሉ በማመቻቸት እንሠራለን ብለዋል፡፡ ቀጣይ የውድድር መድረኮችንም ቢሯቸው እንደሚደግፍ ገልጸዋል፡፡

በምክትል ርእሰ መሥተዳደር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ እና የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) የፈጠራ ምንጮች አነስተኛ የሚመስሉ አስገራሚ ሀሳቦች ናቸው ብለዋል፡፡ ፈጠራ በቴክኖሎጂ ብቻ ሳይኾን በሁሉም ዘርፍ ጭምር መኾኑንም አንስተዋል፡፡ ከተለመደው አስተሳሰብ ወጥቶ ማሰብን እና ኀላፊነትን በመውሰድ እየወደቁ እየተነሱ መሥራትን እንደሚጨምር አንስተዋል፡፡

ዶክተር ሙሉነሽ በፈጠራ ሥራዎች የሀገር ሁለንተናዊ ዘርፍ እንደሚያድግ ጠቅሰው የፈጠራ ተሳታፊዎቹን አመስግነዋል፡፡ በቀጣይም ለሀገር ተስፋ መኾናቸውን ገልጸዋል፡፡ በቀጣይም ልዩ ተሰጥኦ ያላቸውን ተማሪዎች ለማስተማር ዝግጅት መደረጉን አንስተዋል፡፡

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous article“የገጠር ኮሪደር ልማት ሀገርን የመለወጥ ሰፊ ራዕይ የተሰነቀበት ሀገራዊ ውጥን ነው” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)
Next article“ሀገር የምትቀጥለው ሳይሰስቱ ደም እና አጥንታቸውን በሚገብሩ ውድ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ነው” ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)