
ባሕር ዳር: ግንቦት 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከንባታ ዞን አዲሎ ዙሪያ ወረዳ ሀሚዶ ቀበሌ የገጠር ኮሪደር ልማትን አስጀምረዋል።
በተጨማሪም በቀበሌው የሚኖረው አንድ የአርሶ አደር ሞዴል የገጠር መንደርን ጎብኝተናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አርሶ አደሩ ጽዱ፣ ጤናማና ለማየት እጅግ ማራኪ የኾነ የመኖሪያ አካባቢን በመኖሪያ ግቢው ውስጥ በመፍጠር ምሳሌ የሚኾን ሥራ አከናውኗል ብለዋል።
ጽዱ የመኖሪያ ሥፍራን ከመፍጠር ባለፈ በሌማት ትሩፋት እና ጓሮ አትክልት ልማት ላይም ንቁ ተሳተፎ እያድረገ ይገኛል። ይህ ሥራ በሁሉም አካባቢ በትብብር ሊሰፋ ይገባል ነው ያሉት።
በዞኑ ልዩ የተፈጥሮ ገጸ በረከት የኾነው ሀምበርቾ ተራራን በማኅበረሰብ ተሳትፎ የኢኮ ቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ የተከናወኑ ሥራዎችም እጅግ የሚደነቁ መኾናቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።
በተራራው የተገነባው 777 የመወጣጫ ደረጃ አካባቢውን ተደራሽ የመስህብ ስፍራ ያደርገው አድርጎታል። ተራራ መውጣት እና የተለያዩ የአእዋፋት ዝርያዎችን መመልከት የሚወዱ ቱሪስቶች ወደ እዚህ ስፍራ በመምጣት ማራኪ ጊዜን ማሳለፍ ይችላሉ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባጋሩት መልዕክት።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!