
ባሕር ዳር: ግንቦት 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአንድ ሀገር የኢኮኖሚ ዕድገት የጀርባ አጥንት ገቢ ነው። ገቢን በውጤታማነት ለመሠብሠብ አቅምን አሟጦ መጠቀም ይገባል። ክልሉ በበጀት ዓመቱ መሠብሠብ የሚገባውን ግብር ለመሠብሠብ ሁሉም የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ እንደሚገባም ተጠይቋል፡፡
የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ በበጀት ዓመቱ 71 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ በመደበኛ እና በከተማ አገልግሎት ገቢ ለመሠብሠብ አቅዶ ነው ሲንቀሳቀስ የቆየው። እስካኹንም 50 ነጥብ 8 ቢሊዮን በላይ ብር መሠብሠብ መቻሉን የገቢዎች ቢሮ የግብር አወሳሰን አሠባሠብ እና ክትትል የሥራ ሂደት ዳይሬክተር አትንኩት በላይ ገልጸዋል፡፡
ክንውኑ ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ16 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በላይ ብልጫ እንዳለውም ነው የተናገሩት፡፡ የገቢ አሠባሠቡ የቁጥር ዕድገት ይኑረው እንጂ ከሕዝቡ የመልማት ፍላጎት እና ክልሉ ካለው ሀብት አንፃር ሲታይ ብዙ መሥራትን እንደሚጠይቅም አብራርተዋል። ዳይሬክተሩ በበጀት ዓመቱ ከዕቅድ አኳያ ተወስዶ ሲታይ እስከአኹን መሠብሠብ ከነበረበት ገቢ 12 ቢሊዮን ብር መሠብሠብ አልተቻለም ነው ያሉ፡፡
ለዕቅዱ አለመሳካት ደግሞ የሰላም ኹኔታው ግብር ከፋዮችን ለማስከፈል ምቹ ኹኔታ ያለመኖር እና በብዙ የንግድ ዘርፎች ላይ የገበያ መቀዛቀዝ፣ ተንቀሳቅሶ ለመነገድ እና ሸቀጥ አዘዋውሮ ለመሥራት የወቅቱ አስቸጋሪ መኾን፣ ግብር ከፋዩ ለሸጠው ዕቃ እና ለሰጠው አገልግሎት ለተጠቃሚው ደረሰኝ ያለመቁረጥ እና የሕገ- ወጥ ንግድ እየተስፋፋ መምጣቱ እንደ ምክንያት ተነስቷል፡፡
ይህም መንግሥት የኅብረተሰቡን የልማት ፍላጎት ምላሽ ለመስጠት ችግር መፍጠሩንም ነው ያስገነዘቡት። ገቢ በሚገባ አለመሠብሠቡ የነዋሪዎቹን የመልካም አሥተዳደር ጥያቄ እንዳይፈታ ከማድረጉም በተጨማሪ ክልሉ ከሌሎች ክልሎች ጋር ተወዳዳሪ እንዳይኾን ጫና ይፈጥራል ነው ያሉት። ወጭውን በገቢው በመሸፈን በኩል ሁልጊዜ ከድጎማ እንዳይወጣ የሚያደርግ ሥለመኾኑም ነው የጠቆሙት፡፡
የክልሉ መንግሥት ኅብረተሰቡ እያነሳ ያለውን የመልማት ጥያቄ ለመመለስ እንዲችል በተቀናጀ መንገድ ገቢን አሟጦ ለመሠብሠብ እየሠራ እንደኾነም ዳይሬክተሩ አብራርተዋል። በቀጣይ የተሻለ ገቢ በመሠብሠብ በኩል አጋር አካላት እንዲረባረቡም ነው ያሳሰቡት። ግብር ከፋዩም ግብር የሚከፍለው ለራሱ እና ለአካባቢው ልማት መኾኑን አውቆ ግብሩን በወቅቱ በመክፈል፣ ለሸጠው ዕቃ እና ለሰጠው አገልግሎት ለተጠቃሚው ደረሰኝ በመቁረጥ የዜግነት ግዴታውን ሊወጣ ይገባልም ብለዋል።
ሕገ-ወጥ ንግድን እና ሕገ- ወጥነት ላይ ጠንካራ ሕጋዊ ርምጃ በመውሰድ ሕግ ማስከበር ላይ ጥረት መደረግ ይኖርበታልም ነው ያሉት፡፡
ዘጋቢ፦ ሰናይት በየነ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን