
ደብረ ታቦር: ግንቦት 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በደቡብ ጎንደር ዞን ላይ ጋይንት ወረዳ ከጎብጎብ እና ሳሊ ነዋሪዎች ጋር ተወያይተዋል። በውይይቱ የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ፣ የአማራ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ አማረ ሰጤ፣ የአማራ ክልል ሚሊሻ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አስቻለ አላምሬ፣ የደቡብ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ጥላሁን ደጀኔ፣ የ303ኛ ኮር አዣዥ ብርጋዴር ጄኔራል ተሾመ ይመር እና ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎችም ተገኝተዋል።
በውይይቱ የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ የአማራ ሕዝብ ዋና ጥያቄ የሰላም ጥያቄ ነው ብለዋል። ከዚህ የበለጠ ጥያቄ አሁን የለውም ነው ያሉት። ሌላው ጥያቄ የሚመለሰው ከሰላም ጥያቄ በኋላ መኾኑን አንስተዋል። “መጀመሪያ ደስታዬን፣ ሰላሜን እፈልጋለሁ ብላችሁ አቋም ስትይዙ ችግሩ ይፈታል” ብለዋል።
የአካባቢው ችግር እንዲፈታ ከተፈለገ ከአብራካችሁ የወጡ ልጆችን በቃ ማለት አለባችሁ ነው ያሉት። እነርሱን እስካልተቃዎማችሁ ድረስ ችግራችሁ ይራዘማል ብለዋል። የሕዝብ ችግር እና መከራ እንዳይራዘም ጽንፈኞችን መታገል እና በቃ ብሎ ሰላምን ማረጋገጥ እንደሚገባም አመላክተዋል። ሕጻናት እንዳይማሩ ማድረግ እና የትውልድ ቅብብሎሽን ማቋረጥ ወንጀለኝነት ነው፤ ከዚህ በላይ ወንጀል የለም ነው ያሉት። ሰላምን እና በሰላም መኖርን ከመረጣችሁ ለእናንተ መስዋዕትነት እየከፈለ ያለውን የሀገር መከላከያ ሠራዊት እና የክልሉን የጸጥታ ኃይል መደገፍ ይገባችኋልም ብለዋል።
መንግሥት ሰላምን ለማስከበር ሙሉ አቅም እንዳለውም ተናግረዋል። ነገር ግን ቅደሚያ የሚሰጠው ለሰላማዊ አማራጭ ነው ብለዋል። የጋይንት ሕዝብ መገለጫ ያልኾነ ባህሪ እና ድርጊት ያላቸው ሰዎች መስተካከል እንዳለባቸውም ተናግረዋል። ጋይንት መገለጫው ጀግንነት፣ አንድነት እና ክብር ነው ያሉት ኀላፊው ሌብነት እና ዘረፋ ለክብሩ አይመጥኑም፤ የቀደመ ክብሩን ለማስጠበቅ ሰላምን ማረጋገጥ ይገባል ነው ያሉት።
በሰሜኑ ጦርነት በጀግንነት ክብሩን እና አካባቢውን ያስከበረው የጋይንት ሕዝብ አሁንም ዘራፊዎችን አደብ በማስገዛት ሰላሙን ማስከበር አለበት ብለዋል። መንግሥት ለሰላም በሩ ክፍት ነው ያሉት ኀላፊው ልጆቻችሁን እየመከራችሁ በሰላም አምጡ ነው ያሉት። የሃይማኖት አባቶች ለሰላም፣ ለፍቅር እና ለሕዝብ ሲሉ እንዲሠሩም ጠይቀዋል። ፍቅርን እና ሰላምን እንዲሰብኩም አሳስበዋል።
መንግሥት ሰላምን ለማስከበር የተጠናከረ ሕግ የማስከበር ሥራ እንደሚሠራም ተናግረዋል። በየቀኑ ገንዘብ አምጡ እየተባላችሁ ከምትሰቃዩ በአንድነት ለሰላም መነሳት አለባችሁ ብለዋቸዋል። ልጆቻችሁን በግፍ ከበሉ ጠላቶቻችሁ ጋር አብራችሁ መሥራት ለክብራችሁ አይመጥንም ነው ያሉት። ለጋይንት ሕዝብ የሚመጥነው ሰላምን በማጽናት ክቡሩን ማስጠበቅ መኾኑን ተናግረዋል።
የልማት ሥራዎች እንዲሠሩ ሰላማችሁን ማረጋገጥ አለባችሁ ያሉት ኀላፊው መንግሥት ለአካባቢው ልማት ትኩረት እንደሚሰጥም ተናግረዋል። ልማት የሚያስቆሙትን ማውገዝ ካልቻላችሁ ግን ችግሩ አይፈታም ነው ያሉት።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን