
ደብረ ታቦር: ግንቦት 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በደቡብ ጎንደር ዞን ላይ ጋይንት ወረዳ ከጎብጎብ እና ሳሊ ነዋሪዎች ጋር በሰላም ዙሪያ ተወያይተዋል። በውይይቱ የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ፣ የአማራ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ አማረ ሰጤ፣ የአማራ ክልል ሚሊሻ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አስቻለ አላምሬ፣ የደቡብ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ጥላሁን ደጀኔ፣ የ303ኛ ኮር አዣዥ ብርጋዴር ጄኔራል ተሾመ ይመር እና ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎችም ተገኝተዋል።
የአማራ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ አማረ ሰጤ በምክክር እና በውይይት ሰላምን ማስከበር እንደሚገባ ገልጸዋል። ወደ ጫካ የወጡ ኀይሎች አላማ የሌላቸው፣ የሕዝብ ጥያቄን ያልያዙ ናቸው ብለዋል። ራስ ጋይንት የጀግና መውጫ ነው ያሉት ምክትል አፈ ጉባኤው በጀግኖች ምድር የተነሱ ጥቂት ሌቦች እና ወንበዴዎች ሕዝብ እያሰቃዩ ነው ብለዋል።
ብልሆች የሰላም አማራጮችን እየተቀበሉ መኾናቸውንም ገልጸዋል። የአካባቢው ነዋሪዎች በጫካ የሚገኙትን መክረው ለሰላም እንዲያስገቡም ጠይቀዋል። እየቀሙ እና እየዘረፉ መኖር ይበቃል፤ ምከሩ እና ወደ ሰላም ይምጡ ነው ያሉት። መንግሥት የሰላም በሩ ክፍት ነው፤ በሰላም ይግቡ፤ መንግሥት በሰላም ይቀበላል ብለዋል። በሰላም አንገባም በሚሉት ላይ ግን የሕግ ማስከበር ሥራ እንደሚሠራም ነው የተናገሩት።
ሹፌሮችን የሚያግቱ፣ ሀብት የሚዘርፉትን፣ የሚያወድሙትን፣ መከላከል እና አሳልፋችሁ መስጠት ይገባቹሀል ነው ያሉት። መንግሥት የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች እንዲፈቱ እየሠራ መኾኑንም ገልጸዋል። የልማት ሥራዎችን እያከናወኑ መኾኑንም ተናግረዋል። “እናንተ ሰላምን ካስከበራችሁ የልማት ሥራዎች ይቀጥላሉ” ያሉት ምክትል አፈ ጉባኤው የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎችን ለመፍታት በጥሩ ሂደት ላይ መኾናቸውን ነው የተናገሩት። የልማት ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።
የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና ወጣቶች ለሰላም እንዲሠሩም አሳስበዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን