
ደብረ ታቦር: ግንቦት 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በደቡብ ጎንደር ዞን ላይ ጋይንት ወረዳ ከጎብጎብ እና ሳሊ ነዋሪዎች ጋር ተወያይተዋል። በውይይቱ የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ፣ የአማራ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ አማረ ሰጤ፣ የአማራ ክልል ሚሊሻ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አስቻለ አላምሬ፣ የደቡብ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ጥላሁን ደጀኔ፣ የ303ኛ ኮር አዣዥ ብርጋዴር ጄኔራል ተሾመ ይመርን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች ሌቦች አስመርረውናል፣ ሰላም እንዲመጣ እንፈልጋለን ብለዋል። ልጆቻችን ከትምህርት ቤት ተለይተው እየኖሩ ነጋችን አሳስቦናል ጨንቆናል ነው ያሉት። ሕግ ይከበርልን፣ በቀያችን በሰላም እንድንኖር ሰላም ይስፈን እኛም ለሰላም አስተዋጽኦ እናደርጋለን ብለዋል። ግፋ በለው እያሉ ከማዋጋት ይልቅ ተው እያሉ መመለስ እና ሰላምን ማምጣት ለሕዝብ እንደሚበጅም ተናግረዋል።
ግጭት እና ጦርነት ለሕዝብ እንደማይጥቅምም ገልጸዋል። መምከር፣ መዝከር እና ሕዝብን መመለስ ይጠበቅብናል፣ ይሄን እናደርጋለን ነው ያሉት። ለታላቅ ሕዝብ የሚመጥን ታላቅ ታሪክ እንጂ ሌባን እና ወንበዴን መደበቅ አይደለም ብለዋል። የሀገር መከላከያ ሠራዊት እና የክልሉ የጸጥታ ኀይል አንጻራዊ ሰላም እንዲመጣ ማድረጉን ገልጸዋል። ነገር ግን አሁን እንደ ልብ ከአካባቢ ወደ አካባቢ በሰላም ለመንቀሳቀስ ችግር አለ ነው ያሉት። እርስ በእርስ ከመገዳደል በመውጣት ሰላምን ማምጣት እንደሚገባም ተናግረዋል።
ከዚህ በላይ ልጆቻችን ሳይማሩ እንዲኖሩ አንፈቅድም፣ የውጭ ጠላት ሳይመጣ፣ በራሳችን ልጆች መሰቃየት የለብንም ብለዋል። ልጆቻችንን ለሁለት ዓመታት ከትምህርት ገበታ ከማራቅ በላይ ሞት የለም ነው ያሉት። ከውይይት እና ከምክክር ብዙ እንደሚተረፍም ተናግረዋል። መሣሪያ እያነሱ ወደ ጫካ መግባት ብዙዎችን ከማሳጣት ውጭ ሌላ ያመጣው ጥቅም አለመኖሩንም ገልጸዋል። በጫካ የሚገኙ ወገኖችም ችግሮቻቸውን በውይይት እንዲፈቱ ጠይቀዋል። አሁን ካለንብት ችግር የሚያወጣን ቁጭ ብሎ መመካከር ነው ብለዋል።
ሰው በተወለደበት ሀገር ተሰቃይቶ መኖር የለበትም፣ በታሪካችን ማየት የማንፈልገውን ነገር በማየታችን አፍረናል፣ አንገታችን ደፍተናል፣ ይበቃናል፣ ስሞት አፈር ስኾን እያለ የሚያባለው ደግ ሕዝብ በግድ ገንዘብ አምጡ እየተባለ እየተሰቃየ ነው ብለዋል። የሚያሳፍር ድርጊት እየፈጸሙ መኖር አይገባም፣ ተው ብሎ መመለስ ይገባል ነው ያሉት። ትልቁ ዳኝነት ያለው ከሕዝብ ነው ያሉት ተሳታፊዎቹ ሕዝብ ከመከረ እና ከዘከረ ሰላም እንደሚመጣም ተናግረዋል።
መንግሥትም ለሕዝብ ፍትሕ መስጠት እና ማገልገል አለበት ብለዋል። መንግሥትን አሁን የምንጠይቀው ሰላምን እንዲያረጋግጥ እና መኖር እንድንችል እንዲያደርግ ነው፣ ሌላውን ጥያቄ ቆይተን እንጠይቃለን ብለዋል። በጫካ የገቡ ወገኖችን እየመከርን ሰላምን እንዲቀበሉ እንሠራለን ብለዋል። መንግሥት ያቀረበውን የሰላም አማራጭ መቀበል እንደሚገባ ገልጸዋል።
የአማራ ክልል ሚሊሻ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አስቻለ አላምሬ የአማራ ክልል በሰሜኑ ጦርነት ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰበት አስታውሰዋል። ከሰሜኑ ጦርነት ሳያገግም ደግሞ ከውስጡ በወጡ ታጣቂዎች ጉዳት ደርሶበታል ነው ያሉት። የአማራ ሕዝብ ጥያቄ የሰላም ጥያቄ ነው ያሉት ኀላፊው መንግሥት የሕዝብ ጥያቄዎች እንዲፈቱ እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል። የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች ለጦርነት አይጋብዙም ብለዋል። የአማራን ሕዝብ ጥያቄ ይዘን ነው የወጣን የሚሉ ኃይሎች ሃሰተኞች ናቸው፣ የአማራን ሕዝብ ጥያቄ ሳይኾን የራሳቸውን ጥቅም ነው የሚያሳድዱ ብለዋል።
ሰላምን ለማረጋገጥ እና የጸና ለማድረግ ጽንፈኛውን ኃይል እረፍ ማለት ይገባል ብለዋል። የሀገር መከላከያ ሠራዊት እና የክልሉ የጸጥታ ኃይል ሰላምን ለማረጋገጥ እየሠሩ መኾናቸውን ተናግረዋል። መንግሥት በየጊዜው የሰላም ጥሪ እያቀረበ መኾኑን የተናገሩት ኀላፊው ሰላም መሸነፍ አይደለም ነው ያሉት። ችግሮችን በሰላም መፍታት የተሻለው እና አዋጩ መኾኑንም ገልጸዋል።
ሁልጊዜም ሰላምን መስበክ መሸነፍ አለመኾኑንም ተናግረዋል። የሃይማኖት አባቶች መክረው እና ገስጸው እንዲመልሱም ጠይቀዋል። ሰላምን አንፈልግም ባሉት ላይ ግን የሕግ ማስከበር ሥራ እንሠራለን ነው ያሉት። የ303ኛ ኮር አዣዥ ብርጋዴር ጄኔራል ተሾመ ይመር በጥቂት ቡድኖች የአማራ ሕዝብ በታሪኩ አይቶት የማያውቀውን መጤ ባሕል ተሸክሟል ነው ያሉት። የራሱ ልጆች አንገቱን አስደፍተውታል፣ መከራው እንዲበዛ አድርገውበታል፣ ይህ ደግ እና ኩሩ ሕዝብ ሊበቃው ይገባል ብለዋል።
የጠላቶችን ሃሳብ የሚሸከሙ ከአብራኩ የወጡ ልጆቹ ሕዝቡን ጎድቶታል ነው ያሉት። ተቋማቱ እየተዘረፉ ነው፣ ልጆቹ ትምህርት ቤት አይሄዱም፣ ብዙ ነገር እያጣ ነው ብለዋል። ጽንፈኛው ኀይል ከእናንተ በላይ አይደለም ያሉት አዛዡ አናበላህም፣አናጠጣህም ብትሉት፣ ዘረፋ የአማራ ባሕል አይደለም፣ ልጆቻችን መማር አለባቸው ብላችሁ ሰልፍ ብትወጡ ለሰላም ይገባል ብለዋል።
ከዚህ በላይ ስቃይ ይበቃል፣ የትውልድ ክፍተት መፈጠር የለበትም ብላችሁ በቃ በሉ ነው ያሉት። ሰላማዊ አማራጭን እንዲቀበሉ ምክሩ አምቢ ካሉ ግን አሳልፋችሁ ስጡ ብለዋል። የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ያላቸውን ተሰሚነት ተጠቅመው ታጣቂዎች ለሰላም እንዲገቡ እንዲመክሩም አሳስበዋል። ሕዝብ ከዚህ በላይ አንገት እንዳይደፋ የሰላም አማራጭ የማይጠቀሙትን አሳልፋችሁ ስጡ ነው ያሉት።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን