“ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ተቀራርበን የመሥራት ባሕልን እየገነባን ነው” ከንቲባ አዳነች አቤቤ

30

አዲስ አበባ: ግንቦት 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የእርስ በርስ መደማመጥ እና መመካከር ባሕልን በማዳበር ለጋራ ሀገር ግንባታ በትብብር የመሥራት ልምድ ሊጠናከር እንደሚገባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ አስታውቀዋል። የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከአዲስ አበባ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ጋር ተወያይተዋል።

ውይይቱ “ለተረጋጋ የፖለቲካ ሥርዓት እና ባሕል ግንባታ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሚና” በሚል መሪ መልዕክት ነው የተካሄደው። በውይይቱ የተሳታፉ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በከተማዋ እየተከናወኑ ያሉ ሰው ተኮር ልማቶች የሚደነቁ እና ለሌሎች አካባቢዎችም ተሞክሮ መኾን የቻሉ ናቸው ብለዋል።

የኮሪደር ልማት፣ ሕጻናትን መመገብ እና ሳቢና ማራኪ አካባቢዎችን መፍጠር ላይ የተከናዎኑ ተግባራት የሚደነቁ ናቸው ነው ያሉት። በከተማዋ የልማት እና ሌሎች ተግባራት ከአሥተዳደሩ ጋር ተቀራርቦ መሥራት በመቻሉ አዲስ የፖለቲካ ሥርዓትን ፈጥሯል፤ ይህንን አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል።
የኑሮ ውድነት እና ብልሹ አሠራሮች ተፎካካሪ ፓርቲዎች ቢስተካከሉ ብለው ያነሷቸው ሌሎች ሃሳቦች ናቸው።

ዘላቂ ሰላምን በከተማዋ እና በሀገሪቱ ለማምጣት ችግሮች በውይይት ለመፍታት የተጀመረው ልምድ ቢዳብር ብለዋል። የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከለውጡ ወዲህ እንደ ሀገርም ኾነ እንደ አዲስ አበባ ከተማ በገዢው ፓርቲ እና በተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ያለው የፖለቲካ እሳቤ ልዩነት እንደተጠበቀ ኾኖ በሀገራዊ እና በከተማ አቀፍ የጋራ ጉዳዮች ዙሪያ ተግባቦት እየፈጠርን፤ “ተቀራርበን የመሥራት ባሕል እየገነባን ነው” ብለዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች የመንግሥት ሥልጣንን ለመጨበጥ በሕዝብ ይሁንታ ምርጫን ማሸነፍ እንዳለባቸው የሚታወቅ ቢኾንም ብልጽግና ሥልጣን ከያዘ በኋላ አዲስ እና የላቀ የፖለቲካ ባሕል መለማመድ አለብን ከሚል ቁርጠኛ አቋም የተነሳ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በመንግሥት ካቢኔ ውስጥ ጭምር እንዲካተቱ ተደርገው አብረን በመሥራት ላይ ነን ነው ያሉት።

አዲስ የፖለቲካ ባሕልን በተጨባጭ እየገነባን እንገኛለንም በማለት ገልጸዋል። በከተማዋ የሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች የከተማ አሥተዳደሩ ነዋሪዎችን ኑሮ ለማሻሻል ላከናወኗቸው በርካታ የልማት ሥራዎች ማበረታታት መቻላቸው በጎ የዲሞክራሲ ልምምድ ነው ብለዋል። እንደ ከተማ አሥተዳደር የጀመርነውን አዎንታዊ መስተጋብር ማሳለጥ እንዲኹም የሕዝቡን ፍላጎቶች መሠረት ያደረጉ ተግባራትን በፍጥነት እና በጥራት መሥራትን አጠናክረን እንደምንቀጥል እናረጋግጣለን ነው ያሉት።

የፖለቲካ ምህዳሩን ይበልጥ እያሰፋን ለሀገር ሰላም እና ልማት የሚጠቅሙ በርካታ ውጤታማ ሥራዎችን በትብብር እና በጋራ መሥራታችንን አጠናክረን ለመቀጠል መግባባት ላይ እንደተደረሰም ከንቲባዋ ገልጸዋል።

ዘጋቢ: ኢብራሂም ሙሐመድ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous article“ሰማይ ቢቀደድ ሽማግሌ ይሰፋዋል”
Next article“ግፋ በለው እያሉ ከማዋጋት ይልቅ ተው እያሉ መመለስ ለሕዝብ ይበጃል”