
ባሕር ዳር: ግንቦት 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በዓለም ላይ በተለያዩ ጊዜያት በተለያዩ ሀገራት የተከሰቱ ግጭቶች በርካታ የሰው ሕይዎት ከቀጠፉ እና የትየለሌ ንብረት ካወደሙ በኋላ መቋጫቸው ውይይት እና ይቅርታ ነው፡፡ በኢትዮጵያ እዚህም እዚያም የተከሰቱ ግጭቶችም ያለ አሸናፊ እና ተሸናፊ በውይይት እና ይቅርታ በሰላም እንዲፈቱ የሃይማኖት አባቶች ድልድይ በመኾን የተጫወቱት ሚና ከፍተኛ እንደነበር ይነሳል፡፡
ጉዳዩን አስመልክተን ያነጋገርናቸው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ዋና ጸሐፊ እና የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አባል መልአከ ብርሃን ፍስሐ ጥላሁን ግጭቶችን በንግግር በመፍታት ሰላም እንዲሰፍን ከሃይማኖት አባቶች የሚጠበቅ ዐብይ ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡
የሰላም ባለቤት ፈጣሪ ነው ያሉት መልአከ ብርሃን ፍስሐ “ቅዱስ ጳውሎስ ቢቻላችሁስ ከሁሉም ሰው ጋር በሰላም ኑሩ” ማለቱን አስታውሰዋል፡፡ ይህም ማለት ከማንም ሰው ጋር በሰላም መኖር እንደምንችል እየነገረን ነው ብለውናል፡፡ ሰላማዊ አየር መተንፈስ የሚቻለውም ሰላም ሲኖር እንደኾነ አብራርተዋል፡፡
ሰላም የሚመጣውም የሚታጣውም በሰው ልጆች ነው ያሉት መልአከ ብርሃን ፍስሐ የምንተነፍሰው አየር እንኳ ያለሰላም የማናገኘው መኾኑን ካወቅን የሰላም ጠባቂዎች እኛው መኾን አለብን ነው ያሉት፡፡ ግጭቶች በፍቅረ ሲመት እና በፍቅረ ነዋይ እንደሚመጡ ነው መልአከ ብርሃን ፍስሐ ያስገነዘቡት፡፡
ግጭቶችን ለማስቆምም በመጀመሪያ ቤተሰብ ከፍተኛ ኀላፊነት አለበት፡፡ ትምህርት ቤቶችም የግጭትን አስከፊነትን እና የሰላምን አስፈላጊነት ማስተማር ይኖርባቸዋል፡፡ መንግሥትም የመልካም አሥተዳደር ክፍተቶችን በመዝጋት በዚህ መንገድ የሚነሱ ግጭቶች እንዳይኖሩ ማድረግ ይኖርበታል ሲሉ መክረዋል፡፡
”እኛ የሃይማኖት አባቶች በየቤተ- እምነታችን የምናስተምርበት መጽሐፈ ቅዱስ እና ቅዱስ ቁርዓን መጻሕፍት በሚሉት መሠረት ለልጆቻችን ስለ ሰላም ጠቀሜታ፣ የግጭትን አስከፊነት ለየትኛውም አማኝ በማስተማር ግጭቶችን ማድረቅ ይገባናል” ብለዋል፡፡ የትኛውም አማኝ ከመጥፎ ነገር በመታቀብ ሰላም ይሰፍናልና ነው ያሉት፡፡
መልአከ ብርሃን ፍስሐ አክለውም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የጸሎት መጀመሪያው ”የበደለንን ይቅር እንደምንል አቤቱ! ወደ ፈተና አታግባን!” እንደማለቱ እንደሀገር እና ክልል የገጠመው የሰላም እጦት በውይይት፣ ንግግር እና ምክክር ልዩነትን በመፍታት በይቅርታ ሰላም እንዲሰፍን መሥራት ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡
በእኛ በኩል ትናንትም ዛሬም ወደ ፊትም ግጭት እናዳይኖር እና የተከሰቱ አለመግባባቶችም በንግግር እንዲፈቱ፤ አብሮነት እና አንድነት እንዲጎለብት እየሠራን ነው፤ እንሠራለንም ነው ያሉት፡፡ ”ሰማይ ተቀደደ ቢሉት ሽማግሌ ይሰፋዋል” የሚለውን ሀገራዊ ብሂል በመጥቀስ በይቅርታ እና በሽምግልና የማይፈታ ነገር አለመኖሩን መልአከ ብርሃን ፍስሐ አስታውሰዋል፡፡ ሁላችንም ለንግግር ፣ ውይይት እና እርቅ መዘጋጀት ይገባናልም ብለዋል፡፡
የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት የደአዋ እና ትምህርት ዘርፍ ሼህ መሐመድ ኢብራሂም ሀገራችን ተረጋግታ ሕዝቦች በሰላም ውለው እንዲያድሩ ሰላም ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ ዛሬ ላይ በአንዳንድ ቦታዎች የተሟላ ሰላም ባለመኖሩም የእምነት አባቶች በፈለጉት ሰዓት ወጥተው ምዕመናኑን ለመስበክ ሲቸገሩ ይስተዋላል ነው ያሉት፡፡ ይህም የሰላም ዋጋ በምንም ሊተመን አለመቻሉን ቁልጭ አድርጎ ያሳል ብለዋል፡፡
እንደ ሀገር እና ክልል አሁን ላይ የገጠሙት ግጭቶች ወደ ሰላም እንዲመጡ የእምነት አባቶች ሚና ከፍተኛ መኾኑን ተናግረዋል፡፡ በተለይም የእምነት አባቶች ልጆቻቸው እዚህም እዚያም በሚራገቡ ከፋፋይ እና ግጭት ጠንሳሽ ሀሳቦች ውስጥ እንዳይገቡ ማድረግ አለባቸው ነው ያሉት፡፡ የሃይማኖት ተቋማት ሰርክ ሰላምን መስበክ አለባቸው ያሉት ሼህ መሐመድ ለግጭቶች መክሰም ምዕመናን ከዘረኝነት አስተሳሰብ ነጻ መኾን አለባቸው፡፡
አግላይነት ግጭትን ያባብሳል፤ ወደ አንድ ቡድን መለጠፍም ግጭት እንዲሰፋ ያደርጋል፡፡ የእያንዳንዱ ሰው ሃይማኖት ሊለያይ ቢችልም የሃይማኖት አባት ሲኾን ግን ሁሉም ሰው ያለ ልዩነት ልጁን ስለሰላም ማስተማር አለበት ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን በእምነት ብንለያይም ለጋራ ሀገራችን ቁስል መሻር፣ ለግጭቶች መምከን እና ለሰላም መስፈን የሃይማኖት አባቶች ከልጆቻችን ጋር በመወያየት፣ በመመካከር ለለመፍትሄው መሥራት ይገባል ብለዋል፡፡ በዚህ መልኩ ሥንሠራ አሁን የሚስተዋለው ግጭት ተወግዶ ዘላቂ ሰላም የማይሰፍንበት ምክንያት የለም ነው ያሉት፡፡
የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ሀገራዊ የሰላም ጉባዔ ከሰኔ 4 እስከ 5/2017 ዓ.ም በባሕር ዳር ከተማ እንደሚካሄድ ከኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል፡፡
ዘጋቢ:- ሙሉጌታ ሙጨ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን