
ጎንደር: ግንቦት 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ሴቶች የሚገጥሟቸውን ጾታዊ ጥቃት እና ተቋማዊ ጫና ለማቃለል ውጤታማ ሥራ መሠራቱን የአማራ ክልል የሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ አስታውቋል። ከጎንደር ቀጣና ለተውጣጡ ሴት መሪዎች በችግሮች ውስጥም ተኾኖ ፈተናን በመሻገር የማኅበራዊ እና ፓለቲካዊ ተሳትፏቸውን ለማሳደግ የሚያስችል ሥልጠና በጎንደር ከተማ እየተሰጠ ነው።
በመርሐ ግብሩ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የከተማ ልማት ዘርፍ አስተባባሪ እና የክልሉ ከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ አሕመዲን መሐመድ (ዶ.ር)፣ የአማራ ክልል ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኀላፊ ብርቱካን ሲሳይ፣ የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው እና ከፍተኛ የዞን እና የወረዳ ሴት መሪዎች ተሳታፊ ኾነዋል።
ሥልጠናው በክልሉ ያጋጠመው የጸጥታ ችግር በሴቶች ላይ ያመጣውን የሥነ ልቦና ጫና በመቋቋም አሁን ያለውን አንጻራዊ ሰላም ለማስቀጠል እና የአመራር ብቃታቸውን ለማሳደግ ነው ተብሏል። በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የከተማ ልማት ዘርፍ አስተባባሪ እና የክልሉ ከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ አሕመዲን መሐመድ(ዶ.ር) መንግሥት የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ የቀረጸው የአምስት እና የ20 ዓመት ዕቅድን ለማሳካት እየተሠራ ነው ብለዋል።
አሁን የገጠሙ ቀውሶች የተሻለ የመሪነት ዕድልን የሚፈጥሩ በመኾናቸው ሴት መሪዎች ወደ ጥሩ አጋጣሚ ሊለውጡት እንደሚገባ ተናግረዋል። ሴቶች ራስን የመቆጣጠር፣ ከማኅበረሰቡ ጋር የመግባባት አቅማቸው ከፍ ያለ በመኾኑ አቅማቸውን በማሳደግ ክህሎት የተላበሰ መሪ ሊኾኑ ይገባልም ነው ያሉት።
ሴቶች በብልሃት ሀገርን የመምራት ክህሎት ያላቸው መኾኑን የገለጹት የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው ይህንን ተፈጥሯቸውን ለመሪነት ሊጠቀሙበት ይገባል ብለዋል። ሴቶች የሁሉም ነገር መሠረት፣ የጥበብ ማሳያ እና የጥንካሬ ምንጭ ናቸው ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው በኢትዮጵያ ታሪክም እንደ እቴጌ ምንትዋብ ድንቅ የሀገር መሪነት ጥበብ የተላበሱ እና ጥበበኛ ሴቶች ስለመኖራቸው ነው ያነሱት።
በከተማዋ በሚሠሩ የልማት ሥራዎች የሴቶች ተሳትፎ ወሳኝ እንደኾነም ነው ያብራሩት። ሴቶች እና አረጋውያን ከከተማዋ ልማት ተጠቃሚ እንዲኾኑም እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል። ሴቶች የማኅበረሰቡ ግማሽ አካል ቢኾኑም የፓለቲካ እና የማኅበራዊ ተሳትፏቸው አናሳ ኾኖ መቆየቱን የክልሉ ሴቶች እና ሕጻናት ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኀላፊ ብርቱካን ሲሳይ ገልጸዋል።
ሴቶች የሚገጥሟቸውን የተዛቡ አመለካከቶች፣ ጾታዊ ጥቃት እና ተቋማዊ ጫና ለማቃለል የክልሉ ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ውጤታማ ሥራ መሥራቱንም ተናግረዋል። ሴቶች በአመራር ሰጭነት የተሻሉ እንዲኾኑ ወቅቱን የዋጀ የአቅም ግንባታ ሥልጠና በመስጠት በቀጣዩ ምርጫ የሴቶች የተሳትፎ ድርሻ ትልቅ እንዲኾን ከወዲሁ ሥራዎች እየተሠሩ ነው ብለዋል።
ሴት መሪዎች አሁን ላይ ለተፈጠረው አንጻራዊ ሰላም የድርሻቸውን እየተወጡ መኾኑን ገልጸው በግጭቱ ምክንያት ከገጠመው የድባቴ ስሜት እንዲወጡ ሥልጠና መስጠት አስፈላጊ ነው ብለዋል። ሥልጠናው ለሦስት ተከታታይ ቀናት የሚሰጥ ሲኾን የሴቶችን ጽናት እና አይበገሬነታቸውን ከፍ ለማድረግ የተደረገ ውይይት መኾኑንም ኀላፊዋ ገልጸዋል።
ዘጋቢ፦ ዳንኤል ወርቄ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን