
አዲስ አበባ: ግንቦት 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮ ቤልጂየም የቢዝነስ ፎረም በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል። በተለያዩ የኢንዱስትሪ ዘርፎች የሚሠሩ የቤልጂየም አልሚዎች ልዑካን ቡድን በፎረሙ ላይ እየተሳተፉ ሲኾን ከኢትዮጵያ ባለሀብቶች ጋር ውይይት እያደረጉ ነው።
ፎረሙ በኢትዮጵያ ያሉትን የኢንቨስትመንት አማራጮችን ለማስተዋወቅ ምቹ አጋጣሚ እንደሚፈጥርም ተገልጿል።
በውይይቱ የተገኙት የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ መንግሥት የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ እና ለማጠናከር የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራ ነው ብለዋል። የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ለዚህ ዘርፍ መጠናከር ትልቅ ዕድል ይዞ እንደመጣ ገልጸው በርካታ የውጭ ባለሀብቶችን እየሳበ እንደኾነም አስረድተዋል።
በኢትዮጵያ የቤልጂየም አምባሳደር አኔሊስ ቨርስቲቼልን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የኢንቨስትመንት ዕድሎችን እያሠፋ መኾኑን ተናግረዋል። በኢትዮጵያ እና በቤልጂየም መካከል ያለውን 120 ዓመታት ያስቆጠረ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በኢንቨስትመንትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
ለሁለት ቀናት በሚቆየው በዚህ ፎረም የቤልጂዬም ባለሀብቶች ቴክኖሎጂ፣ ግብርና እና ታዳሽ ኀይልን ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች ልምዳቸውን ያካፍላሉ ተብሏል።
ዘጋቢ፦ መሠረት መቅጫ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን