የሰላም አማራጭ የብልሆች ምርጫ ነው።

23

ደብረታቦር: ግንቦት 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በደቡብ ጎንደር ዞን ላይ ጋይንት ወረዳ ከጎብጎብ እና ሳሊ ነዋሪዎች ጋር እየተወያዩ ነው። በውይይቱ የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ፣ የአማራ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ አማረ ሰጤ፣ የአማራ ክልል ሚሊሻ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አስቻለ አላምሬ፣ የደቡብ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ጥላሁን ደጀኔ፣ የ303ኛ ኮር አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል ተሾመ ይመርን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።

በውይይቱ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የደቡብ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ጥላሁን ደጀኔ ለሰላማችን ሊበጅ የሚችል ውይይት በማድረግ የመፍትሔ ሀሳብ ማበጀት ይገባል ብለዋል። ሰላማችን ያሳጣንን የጽንፈኝነት አስተሳሰብ እና ተግባርን ማስወገድም ይገባል ነው ያሉት። ጽንፈኛው በሕዝብ ላይ የከፋ ጉዳት ማደረሱንም ተናግረዋል።

ሰላምን በማረጋገጥ ከሀገር ልማት የጋይንት ሕዝብም ተቋዳሽ መኾን አለበት ነው ያሉት። ጽንፈኝነት የኋላቀርነት አስተሳሰብ መኾኑን አንስተዋል። ጽንፈኞች ለሌሎች ታዛዥ በመኾን የአማራ ክልል ሕዝብ በልማት እንዲያንስ እያደረጉ መኾኑን ገልጸዋል። ልጆቹ እንዳይማሩ የሚያደርግ፣ የክልሉ ሕዝብ አልምቶ እንዳያድግ የሚያደርግ የሕዝብ ጠላት ነው ብለዋል።

ጽንፈኛው በላይ ጋይንት ሕዝብ ጥፋት ማድረሱንም ገልጸዋል። ጽንፈኝነትን መታገል ካልቻላችሁ ሰላማችሁን ማረጋገጥ እና ልማትን ማፋጠን አትችሉም ነው ያሉት። ከውስብስብ ችግር ለመውጣት እና የተሻለ ልማት ለመፍጠር ጽንፈኝነትን ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል። ሰላማችን ራሳችን ማጽናት እና አቅም መገንባት ይገባል ነው ያሉት። ሰላም መተኪያ የሌለው ውድ ሀብት መኾኑንም ገልጸዋል። ሰላም ሲታጣ የታጣው ብዙ መኾኑን ነው የተናገሩት።

ጽንፈኞች በአማራ ሕዝብ ጥያቄ ጭንብል የአማራን ሕዝብ ለችግር የሚዳርጉ ናቸው ብለዋል። በዞኑ በርካታ ታጣቂዎች የሰላም አማራጮችን እየተጠቀሙ መኾናቸውን ገልጸዋል። እንዲህ አይነቱ መልካም ሂደት የሚደገፍ መኾኑንም ተናግረዋል። የሰላም አማራጭ የብልሆች ምርጫ ነው ብለዋል። መንግሥትም በሆደ ሰፊነት የሰላም አማራጮችን በማመቻቸት እየተቀበለ መኾኑን ገልጸዋል።

ሌሎች የታጠቁ ኀይሎች ሰላማዊ አማራጮችን እንዲቀበሉ የሀገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶችን መምከር እና መመለስ አለባቸው ነው ያሉት። ከኢትዮጵያዊነት ማማ የማይወርደው የጋይንት ሕዝብ ጽንፈኝነትን መታገል ይገባዋልም ብለዋል። የሀገር መከላከያ ሠራዊት እና የክልሉ የጸጥታ ኀይል በሠራው ሥራ ዞኑ አንጻራዊ ሰላም ላይ መኾኑንም ገልጸዋል። የሀገር መከላከያ ሠራዊት እና የክልሉ የጸጥታ ኀይሎች ለሠሩት ሥራ ምሥጋና አቅርበዋል።

ሰላምን ለማጽናት እና ዘላቂ ለማድረግ የራሱን ሰላም በራሱ የሚጠብቅ ማኅበረሰብ ያስፈልጋል ብለዋል። መንግሥት የታጠቁ ኀይሎች በሰላም እንዲገቡ ይፈልጋል፣ እምቢ ባሉት ላይ ግን የተቀናጀ የሕግ ማስከበር ሥራ ይሠራል ነው ያሉት። የዞኑን ሰላም ለማረጋገጥ እንደሚሠራም ተናግረዋል። ከዕውነት ጎን በመቆም፣ ሰላምን በማስቀደም መሥራት እንደሚገባም ገልጸዋል።

ሰላም የሌለው ሕዝብ በድህነት ውስጥ እንደሚኖርም ተናግረዋል። ሰላም እንዲሰፍን እና የሕግ የበላይነት እንዲጠናከር የበኩላቸውን እንዲወጡም አሳስበዋል። የጋይንት ሕዝብ ሰላሙን በማረጋገጥ የከፍታ ታሪኩን ማስቀጠል እንደሚገባውም ነው የተናገሩት።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየቅጥር ማስታወቂያ
Next article“መንግሥት የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ እየሠራ ነው” የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ