
ባሕር ዳር: ግንቦት 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የፈለገ ሕይወት አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል “ከኪዩር ብላይንድነስ ፕሮጀክት” ጋር በመተባበር የዐይን ሞራ ግርዶሽ ቀዶ ጥገና ህክምና እንደሚሰጥ አስታውቋል። የችግሩ ተጠቂ የኾኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች በሆስፒታሉ ተገኝተው የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲኾኑም ሆስፒታሉ ጥሪ አቅርቧል።
የፈለገ ሕይወት አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል “ከኪዩር ብላይንድነስ ፕሮጀክት” ጋር በመተባበር የዐይን ሞራ ግርዶሽ የነጻ ሕክምና እንደሚሰጥ የሆስፒታሉ የዐይን ህክምና ክፍል አሥተባባሪ ድረስ አለማየሁ ገልጸዋል። ህክምናው ከሰኔ 2/2017 እስከ ሰኔ 7/2017 ዓ.ም ባሉት ተከታታይ ቀናት የሚሠጥ ይኾናል ብለዋል። እስከ አኹንም 550 ደንበኞች ተለይተዋል ነው ያሉት አሥተባባሪው።
የችግሩ ተጠቂ የኾኑ አዲስ ተገልጋዮች በሆስፒታሉ ተገኝተው የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መኾን እንደሚችሉም ነው የገለጹት። የዐይን ሞራ ግርዶሽ በኢትዮጵያም ኾነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዓይነ ስውርነትን የሚያስከትል በሽታ ነው፤ ቀዶ ጥገና ደግሞ ዋናው መፍትሔው ነው ብለዋል።
ሆስፒታሉ ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ ከ20 ጊዜ በላይ የዐይን ህክምና ሰጥቷል ነው ያሉት። በዚህም ከ12 ሺህ 500 በላይ ሰዎች አገልግሎቱን ማግኘታቸውን የሆስፒታሉ የዐይን ሕክምና ክፍል መረጃ ያሳያል።
ዘጋቢ: ዳግማዊ ተሠራ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን