የበርሃ አንበጣ መስፋፋቱ ከኮሮና ቫይረስ ስርጭት ጋር ተያይዞ ሳይገታ ከቀጠለ እስከ 30 ሚሊዮን ሕዝብ ለተረጅነት እንደሚጋለጥ አቶ አብርሃም አለኸኝ ገለጹ፡፡

302

ባሕርዳር፡ ግንቦት 17/2012 ዓ.ም (አብመድ) ወጣቱ ለሕዝብ ራሱን አሳልፎ በመስጠት በችግሩ ጊዜ ሁሉ ቀድሞ መድረስ እንዳለበት የብልፅግና ፓርቲ የወጣቶች ሊግ አሳሰበ፡፡

የወቅቱ ዓለም አቀፍ የጤና ስጋት የሆነውን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጨምሮ ወጣቶች በኅብረተሰቡ የምጣኔ ሀብታዊ፣ ፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ ችግሮች ላይ ድጋፍ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ በአካባቢ ጥበቃ ሥራዎች፣ የአቅመ ደካሞችን መጠለያ በማደስ፣ በማሳ ላይ ሥራ በመሳተፍ፣ በደም ልገሳ እና በኮሮና ቫይረስ ስርጭት መከላከል የግንዛቤ ፈጠራ ሥራዎች ወጣቶች ተኪ የሌለው የበጎ ፈቃድ ሥራዎችን እያከናወኑ ነው፡፡

በአማራ ክልል ብልፅግና ፓርቲ የወጣቶች ሊግ የውይይት መድረክ ተዘጋጅቷል፡፡ በውይይቱ የቀጣዩን ክረምት ወራት የወጣቶችን የበጎ ፈቃድ አገልግሎት አቅጣጫ ያስቀምጣል ተብሏል፤ የእስካሁኑን የኮሮና ቫይረስ ስርጭት የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ ይገመግማል ተብሎም ይጠበቃል፡፡ በውይይት መድረኩ መክፈቻ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ብልፅግና ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አብርሃም አለኽኝ ወጣቱ ለሕዝብ ራሱን አሳልፎ በመስጠት በችግሩ ጊዜ ሁሉ ቀድሞ መድረስ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

“በአሁኑ ወቅት በሀገራችን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ገጥመውናል” ያሉት አቶ አብርሃም ችግሮቹን በብቃት ተሻግሮ ነገ ላይ ለመድረስ የወጣቱ ሚና ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ካለፈው ክረምት ጀምሮ ስርጭት በጀመረው የበርሃ አንበጣ ከ3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደታጣም አስታውሰዋል፡፡ የበርሃ አንበጣ ስርጭቱ ከኮሮና ቫይረስ ስርጭት ጋር ተያይዞ ችግሮቹ እንዳሉ የሚቀጥሉ ከሆነ በሚቀጥለው ዓመት በሀገራችን ከ25 እስከ 30 ሚሊዮን ሕዝብ ድጋፍ እንደሚፈልግ ተናግረዋል፡፡ እንደ አቶ አብርሃም ገለፃ ችግሮቹን በብቃት ለማለፍ በክልሉ የሚገኙት ከ50 ሺህ በላይ የወጣት ሊግ መሪዎች ድርብ ተልዕኮ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡ የኮሮና ቫይረስ ስርጭን ለመግታት በወጣቶች በርካታ ሥራዎች መሠራታቸውን ጠቅሰዋል፡፡ “የሚፈለገው ለውጥ ግን ገና አልመጣም” ያሉት አቶ አብርሃም በቀጣይ ጊዜያት የግንዛቤ ፈጠራ ሥራው ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

ባለፉት ወራት በኮሮና ቫይረስ ስርጭት የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ ላይ የወጣቶች ሚና ከፍተኛ እንደነበር አንስተዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በክልሉ በተከሰተው የደም እጥረት ከ34 ሺህ በላይ የኅብረተሰብ ክፍል በደም ልገሳ ተሳትፏል ተብሏል፡፡ የአማራ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ጋሻው ተቀባ ከ2 ሺህ በላይ የወጣት ሊግ መሪዎች እና የወጣት አደረጃጀቶች በደም ልገሳው ተሳታፊ መሆናቸን ጠቅሰዋል፡፡

በውይይቱ ከ15 ዞኖች የተውጣጡ የብልፅግና ፓርቲ የወጣቶች ሊግ መሪዎች እየተሳተፉ ነው፡፡ በውይይቱም በቀጣዩ የክረምት ወራት ለሚካሄዱ የወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት አፈፃፀም አቅጣጫ ያስቀምጣሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡

Previous articleበ73 ተጨማሪ ሰዎች ላይ የኮሮና ቫይረስ ተገኘ፤ 31 ሰዎች የጉዞ ታሪክ የላቸውም፤ በበሽታው ከተያዙት ጋር ንክኪ ስለመኖራቸውም አልተረጋገጠም፡፡
Next articleእስከ 12 ሺህ የሚደርሱ ተፈናቃይ ቤተሰቦች ዛሬ ወደ ቀያቸው እየተመለሱ ነው።