“ሰላም በአንድ ወገን አይመጣም” የአንጎት ወረዳ ነዋሪዎች

18

ወልድያ: ግንቦት 24/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የክልል እና የዞን ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በሰሜን ወሎ ዞን ከአንጎት ወረዳ ሕዝብ ጋር በአሁንተገኝ ከተማ ውይይት አካሂደዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በሕዝብ ጥያቄ አስመላሽ ስም የተደራጁ ሌቦች አካባቢያችንን እያመሱት ነው ብለዋል። ሰው እያገቱ በገንዘብ እየተደራደሩ እንደኾነም ነው በውይይቱ ላይ ያነሱት።

ገንዘቡ የሚገባው በባንክ ሒሳብ ቁጥር ስለኾነ መንግሥት ይህን ተከታትሎ ተጠያቂ ያድርግ ነው ያሉት።

የሰሜን ወሎ ሕዝብ የጦርነትን ሰቆቃ በተግባር ያየ ነውና የሚነግረው አይፈልግም ያሉት ነዋሪዎቹ “ሰላም በአንድ ወገን አይመጣም” ብለዋል። መንግሥትም የድርሻውን ይውሰድ እኛም እንደ ሕዝብ የድርሻችንን እንወስዳለን ነው ያሉት።

አለመግባባትን የምንፈታበትን ጥበብ አሟጠን ተጠቅመን ሰላምን ለማጽናት እንሠራለን ብለዋል። መንግሥትም ፖለቲካዊ ችግሮችን በፍጥነት ይፍታ ሲሉ ጠይቀዋል።

የሰሜን ወሎ ዞን አሥተዳዳሪ አራጌ ይመር ኅብረተሰቡ በጽንፈኞች አመለካከት እንዳይደናገር አሳስበዋል።
የአንጎት ወረዳ ሕዝብ የአካባቢውን ሰላም እንደቀድሞው ሁሉ ጠብቆ በማጽናት ለሚጠይቃቸው የልማት ሥራዎች እንዲፈጸሙለት ተባባሪ ይሁን ብለዋል።

የሰሜን ምሥራቅ ዕዝ ምክትል አዛዥ ሜጄር ጄኔራል ሻምበል ፈረደ ጫካ ያሉት ጽንፈኞች የፖለቲካ አጀንዳ የሌላቸው ዘራፊዎች ናቸው ብለዋል።

ሕዝቡ የጽንፈኞችን አስተሳሰብ እና አደረጃጀት ተረድቶ ሊያወግዛቸው ይገባል ሲሉም አሳስበዋል።

ለአካባቢያችሁ ሰላም መጽናት ሰፊው ድርሻ የአንጎት ወረዳ ሕዝብ በመኾኑ ሚናችሁን በአግባቡ እንድትወጡ ነው ያሉት።

በውይይቱ ላይ የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)፣ የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ አደረጃጀት ዘርፍ ኀላፊ ፍስሃ ደሳለኝ፣ የሰሜን ወሎ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አራጌ ይመር እና የሰሜን ምሥራቅ ዕዝ ምክትል አዛዥ ሜጄር ጄኔራል ሻምበል ፈረደ ተገኝተዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleበሕግ እና በፍትሕ ከሚያምን ሥልጡን ማኅበረሰብ የሚጠበቀው አጥፊን እንዲጠየቅ ማድረግ ነው።
Next articleየጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ከፍተኛ ልዑክ ከሱዳኑ ጀኔራል አብዱል ፈታህ አል ቡርሃን ጋር ተገናኙ።