
ወልድያ: ግንቦት 24/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የክልል እና የዞን ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በሰሜን ወሎ ዞን ከአንጎት ወረዳ ሕዝቦች ጋር በአሁንተገኝ ከተማ ውይይት አካሂደዋል።
የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ አደረጃጀት ዘርፍ ኀላፊ ፍስሐ ደሳለኝ መንግሥት ችግሩን በሰላም ለመፍታት ብዙ እርቀት ሄዷል ብለዋል።
ጽንፈኛው ቡድን ሕዝብን መከራ እያበላ ያለ፤ የአማራ ሕዝብ ጥያቄ እንዳይፈታ እየታገለ ያለ እና የባዕዳን አጀንዳ ተሸካሚ ነው ብለዋል። ሰላምን የሚሻ ሕዝብ ደግሞ ከመደናገር ወጥቶ የጽንፈኛውን ቡድን አስተሳሰብ ሊያወግዝ ይገባል ነው ያሉት።
“በሕግ እና በፍትሕ ከሚያምን ሥልጡን ማኅበረሰብ የሚጠበቀው አጥፊን እንዲጠየቅ ማድረግ ነው” ያሉት ኀላፊው ያጠፋን በይቅርታ አስተምሮ ማለፍም ለሰላም የሚከፍ ዋጋ በመኾኑ መንግሥት ምንም ቢያጠፉ ለይቅርታ ዛሬም በሩ ክፍት ነው ብለዋል።
ጫካ ያሉት ጽንፈኞች ከአማራ አብራክ የወጡ ናቸው ነው ያሉት። የአንጎት ሕዝብም እንደ ሕዝብ ማኅበረሰባዊ እሴቱን ተጠቅሞ ሰላምን ለማጽናት የድርሻውን ሊወጣ ይገባል ብለዋል።
በውይይቱ የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)፣ የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ አደረጃጀት ዘርፍ ኀላፊ ፍስሐ ደሳለኝ፣ የሰሜን ወሎ ዞን አሥተዳዳሪ አራጌ ይመር እና የሰሜን ምሥራቅ ዕዝ ምክትል አዛዥ ሜጄር ጄኔራል ሻምበል ፈረደ ተገኝተዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን