
ባሕር ዳር: ግንቦት 24/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በደቡብ ጎንደር ዞን ታች ጋይንት ወረዳ በአርብ ገበያ ከተማ ከሕዝብ ጋር ተወያይተዋል።
በውይይቱ የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ፣ የአማራ ክልል ምክር ቤት ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ አማረ ሰጤ፣ የአማራ ክልል ሚሊሻ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አስቻለ አላምሬ፣ የደቡብ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ጥላሁን ደጀኔ፣ የ303ኛ ኮር አዣዥ ብርጋዴር ጄኔራል ተሾመ ይመር ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ አሁን ሰላም የተፈጠረው መስዋዕትነት በከፈሉ ጀግኖች ነው፣ መስዋዕትነት የከፈሉ ጀግኖችን እንዳትረሱ አደራ ብለዋል። ለሀገር እና ለሕዝብ ሲሉ እውነትን ይዘው ያለፉ ጀግኖችን ማስታወስ፣ ማክበር እና መዘከር እንደሚገባም ገልጸዋል።
በክልሉ በተፈጠረው ግጭት ምክንያት ዛሬ ላይ ያልተጎዳ ሰው የለም ያሉት ኀላፊው ችግሩ በየሁሉም ቤት ገብቷል፣ ብዙዎች አዝነዋል፣ ተጎድተዋል ነው ያሉት።
የታች ጋይንት ሕዝብ ባለፉት ጊዜያት በልማት ተጠቃሚ ያልኾነው ሰላም ስለሌለ መኾኑንም ገልጸዋል። ሰላም እንዳይኖር ያደረጉ ጽንፈኞችን ሃሳብ ተረድቶ በቃችሁ የማይል ካለ ሕዝብ እንዲሰቃይ የሚፈልግ መኾኑን ነው የተናገሩት። ዓላማቸው ሕዝብ እንደማይጠቅም፣ ለወገን እንደማይኾን፣ ጥያቄ እንዳማያስመልስ፣ ልማት እንደማያመጣ ተረድቶ በቃ ማለት እንደሚገባም አሳስበዋል።
ጽንፈኞችን አስቀድሞ ተው ብላችሁ ቢኾን ኖሮ ይህ ሁሉ በደል ባልደረሰ ነበር ነው ያሉት። አርሶ አደሮች እየተሰቃዩ፣ ሃብት እና ንብረታቸው እየተዘረፈ እና እየተንገላቱ መኾናቸውንም ገልጸዋል።
“አርሳችሁ እንዳትበሉ የሚያደርጋችሁን፣ በጉሮሯችሁ ላይ የመጣውን ኀይል በቃህ ብላችሁ መተጋል አለባችሁ” ነው ያሉት። ሕጻናት እንዳይማሩ የሚያደርገውን ኃይል መታገል አለባችሁ ያሉት ኀላፊው ያልተማረ ሕዝብ በደህነት ነው የሚኖረው፣ ይህን በመረዳት ትምህርት የሚዘጋውን ኃይል ፊት ለፊት መታገል አለባችሁ ብለዋል።
የመንግድ ፕሮጀክቶች እና ሌሎች ልማቶች እንዳይለሙ የሚያደርጉትን ታገሏቸው፣ የልማት ሥራዎችን ያስቆሙት ጽንፈኞች ናቸው፣ በቃችሁ በሏቸው ነው ያሉት። ጽንፈኞችን ተው ብላችሁ ካስቆማችሁ ልማቱ በአጭር ጊዜ ይሳካል ብለዋል።
ከሕዝብ እና ከሀገር ጠላቶች ጋር የሚሠሩ ወንበዴዎችን ማጉረስ እና መደበቅ ነውር መኾኑንም ገልጸዋል። የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች መክረው እንዲመልሱም ጠይቀዋል።
መንግሥት የታጠቁ ኃይሎች ሞት እና እንግልት ሳይኖር በሰላም እንዲገቡ ይፈልጋል፣ አቋም ይዛችሁ ልጆቻችሁን መክራችሁ አስገቡ ነው ያሉት። ለሰላም እምቢ ያለውን ግን ሕግ የማስከበር ሥራ እንሠራለን ብለዋል።
ሕግ የማስከበር ሥራ ሲሠራ ሕዝቡ ከመንግሥት ጎን መቆም አለበት ነው ያሉት። ጽንፈኞች የተነሱት በመንግሥት ላይ ብቻ አይደለም ያሉት ኀላፊው የተነሱት በእናንተ ላይም ነው፣ ልጆቻችሁ እንዳይማሩ፣ ልማት እንዳይሠራ፣ ጥሬ እቃ እንዳይገባ እያደረጉ ነው፣ በቃ ብላችሁ ተነሱ፣ ተመካከሩ፣ ተው በሏቸው ብለዋል።
ስለ እውነት ብሎ መስዋዕትነት የከፈለ በታሪክ ሲወሳ እንደሚኖርም ገልጸዋል። ቸር እና ጀግና የኾነው የጋይንት ሕዝብ ሰላሙን አስጠብቆ የራሱን ታሪክ መሥራት አለበት ነው ያሉት። የአባቶችን ታሪክ ብቻ እየነገሩ መኖር እንደማይገባ እና በራስ ዘመን የራስን ታሪክ መሥራት እንደሚያስፈልግ ነው የተናገሩት።
ተማምላችሁ፣ ስለ እውነት ብላችሁ ምከሩ፣ በሰላምን ስበኩ፣ የራሳችሁን ሰላም አስጠብቁ ብለዋል በመልዕክታቸው።
ሕዝብ ከመንግሥት ጎን ከቆመ ታላቅ ታሪክ እንደሚሠራም ተናግረዋል። “በሰሜኑ ጦርነት በጀግንነት እና በአንድነት ክብራችሁን እንዳስጠበቃችሁ ሁሉ አሁንም ክብራችሁን አስጠብቁ፣ ሽልማታችሁ ክብራችሁ ነው” ብለዋል።
ለሰላም የሚገቡትን በሰላም እንዲገቡ እንዲመክሩ በሰላም የማይገቡትን ደግሞ አሳልፈው እንዲሰጡም አሳስበዋል። በአካባቢያቸው ስለ ሰላም እንዲወያዩ፣ የአካባቢያቸውን ሰላም እንዲያስጠብቁ እና ከመንግሥት ጋር በጋራ እንዲሠሩም አስገንዝበዋል። አሁን የተጀመረው ሰላም ተጠናክሮ እንዲቀጥል እንደሚሠራም አመላክተዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!