“የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ያከናወናቸው የልማት ተግባራት የሚደነቁ ናቸው” የቋሚ ኮሚቴ አባላት

18

ደብረ ብርሃን: ግንቦት 24/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ምክር ቤት የቋሚ ኮሚቴዎች ቡድን በደብረ ብርሃን ከተማ የተከናወኑ የልማት ተግባራትን ከከተማ አሥተዳደሩ ጋር ገምግሟል።

የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት በበጀት ዓመቱ የኅብረተሰቡን ተሳትፎ በመጠቀም በርካታ የልማት ሥራዎች ተሠርተዋል ብለዋል።

ከተማዋ የምትታወቅበትን የኢንዱስትሪ ዘርፍ በማስፋት ኢንቨስትመንቱ በገበያ ማረጋጋት እና በሥራ ዕድል ፈጠራ ዘርፍ የበኩሉን እንዲወጣ እየተደረገ እንደኾነ ነው የተናገሩት።

ለወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ ዘርፎችን በመለየት በአምራች፣ በከተማ ግብርና እና በአገልግሎት ዘርፎች ተጠቃሚ እንዲኾኑ እየተደረገ ስለመኾኑ ለቋሚ ኮሚቴ አባላቱ አብራርተውላቸዋል።

በክልሉ ምክር ቤት የበጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሀናን አብዱ የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ያከናወናቸው የልማት ተግባራት የሚደነቁ ናቸው ብለዋል።

የአረጋዊያን እና አቅመ ደካማ ወገኖችን ትኩረት ያደረጉ ተግባራት ለሌሎች አካባቢዎችም በምሳሌነት የሚነሱ ናቸው ነው ያሉት።

ከተማ አሥተዳደሩ በመሠረተ ልማት ዝርጋታ ላይ ማኅበረሰቡን አሳትፎ የሠራቸው ተግባራትም መጠናከር አለባቸው ብለዋል።

የከተማዋን ገቢ የመሰብሰብ አቅም አሟጦ በመጠቀም ረገድ መሻሻል እንደሚገባውም በግምገማው ላይ ተነስቷል።

ከተማዋ ለነዋሪዎቿ ምቹ እንድትኾን ለማድረግ ከጽዳት እና ውበት ጋር የተያያዙ ሥራዎች ተሻሽለው መሠራት እንደሚገባቸውም ተመላክቷል።

በደብረ ብርሃን ከተማ የደረቅ እና ፍሳሽ ቆሻሻ ማስወገጃ እየተገነባ በመኾኑ ችግሩ በአጭር ጊዜ እንደሚፈታም ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል።

በከተማዋ የሚታየው ከፍተኛ የኾነ የትራንስፖርት ችግር እንዲቀረፍም አቅጣጫ ተሰጥቷል። ከታሪፍ በላይ ማስከፈል እና የስምሪት ችግሮች መፈታት አለባቸው ነው የተባለው።

ሕገ ወጥነትን በመከላከል ረገድ እየተሠራ ያለው ተግባር መልካም አፈጻጸም ያለው ነው፤ በሁሉም ዘርፍ ስኬታማ ተግባርን ለማከናወን ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ ላይ መሥራት እንደሚገባም በግምገማው ተነስቷል።

ዘጋቢ: ሥነ ጊዮርጊስ ከበደ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous article“ጀግና ማለት ሰላምን መርጦ የሕዝብን ጥያቄ የሚያከብር ነው” ምክትል አፈጉባኤ አማረ ሰጤ
Next article“ሽልማታችሁ ክብራችሁ ነው” አቶ ይርጋ ሲሳይ