
ደብረ ታቦር: ግንቦት 24/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በደቡብ ጎንደር ዞን ታች ጋይንት ወረዳ በአርብ ገበያ ከተማ ከሕዝብ ጋር ተወያይተዋል።
በውይይቱ የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ፣ የአማራ ክልል ምክር ቤት ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ አማረ ሰጤ፣ የአማራ ክልል ሚሊሻ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አስቻለ አላምሬ፣ የደቡብ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ጥላሁን ደጀኔ፣ የ303ኛ ኮር አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል ተሾመ ይመር ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎችም በገብርዬ ምድር፣ በእነዚያ ጀግኖች የትውልድ ሥፍራ ከኢትዮጵያዊነት ያነሰ አስተሳሰብ አይጠቅምም፣ አንቀበለውም፤ መለያችን እና መታወቂያችን ከፍታ ነውና ብለዋል።
ጦርነት በቃን፣ እንባ በቃን፣ ግጭት በቃን፣ ግጭት የሰጠን የወንድም ማጣት ነው፣ ከዚህ በኋላ ወንድሞቻችን ማጣት አንፈልግም፤ ሰላም ይምጣ፣ ልጆቻችን እንምከር ብለዋል።
ሰላም አስፈላጊ ነው፤ ከኢትዮጵያ እና ከኢትዮጵያዊነት ማማ ላይ ዝቅ ለማይለው የጋይንት ሕዝብ የእርስ በእርስ ግጭት አያምርበትም፣ አይመጥነውም ነው ያሉት።
ሰላም ከሌለ ምንም ነገር የለም፣ ግጭቱ እስካሁን የቆዬው ሁሉም ሰው በአንድነት ለሰላም ስላልተነሳ ነው፣ ከዚህ በኋላ በቃን ለሰላም በጋራ መነሳት አለብን ነው ያሉት። ሁሉም የታጠቁ ኃይሎችን እየመከረ ለሰላም ማምጣት፣ እምቢ ያለውን ደግሞ እያጋለጡ መስጠት ይገባል ብለዋል።
የሀገር መከላከያ ሠራዊት የኢትዮጵያ መከታ እና አለኝታ ነው፣ ይህን ጀግና ሠራዊት እናግዘውና በአጭር ጊዜ ሰላማችን እናረጋግጥ ነው ያሉት። አላግዘው ብለን እንጂ ጀግናው ሠራዊት በቀናት ውስጥ ሰላማችንን ያስከብርልን ነበር ብለዋል።
አንወቅሳችሁም፣ እንኳን ደህና መጣችሁ፣ ቀዳሚው ሰላም ነው፣ እንኳን ለሰላም ልትመክሩ፣ በሰላም መጣችሁ። መጀመሪያ የምንጠይቃችሁ ሰላም እንዲመጣ ነው፤ ሰላም ሳይረጋገጥ ምንም አንጠይቃችሁም፤ ሰላም በተረጋገጠ ጊዜ ግን ልማት እንፈልጋለን፣ የተጀመሩት እንዲጠናቀቁ እንጠይቃለን ነው ያሉት። አሁን ላይ የለሙትን የሚያፈርሱ አሉ፣ ይሄን መጠበቅ ይገባል ብለዋል።
የተጀመረው ሰላም እንዲጠናከር እስከ መስዋዕትነት ድረስ የዘለቀ ድጋፍ እንደሚያደርጉም ገልጸዋል። ሰላምን በማረጋገጥ የሕዝብን ጥያቄ መመለስ እንደሚገባም ተናግረዋል።
የአማራ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ አማረ ሰጤ ጽንፈኛው ኃይል በክልሉ ላይ መጠነ ሰፊ ጉዳት አድርሷል ብለዋል። የሃይማኖት አባቶችን እና የሀገር ሽማግሌዎችን የማያከብር፣ የሕዝብ እሴትን የሚጥስ ለሕዝብ የማይጠቅም ነው ብለዋል።
የአማራን ሕዝብ ጥያቄ እንደ ሽፋን ይዞ ሕዝብን የሚያሰቃይ ቡድን መኾኑንም ገልጸዋል። ሰላም ወሳኝ መኾኑን አውቃችሁ ለሰላም ልትሠሩ ይገባል ነው ያሉት።
የክልሉ መንግሥት የሰላም ጥሪ በተደጋጋሚ ማቅረቡን የተናገሩት ምክትል አፈ ጉባኤው በርካታ ኃይሎችም ለሰላም መግባታቸውን ገልጸዋል። አሁንም መንግሥት ለሰላም በሩ ክፍት ነው ብለዋል። በግጭት የሚፈታ ጥያቄ አለመኖሩንም ተናግረዋል።
“ጀግና ማለት ሰላምን መርጦ የሕዝብን ጥያቄ የሚያከብር ነው” ያሉት ምክትል አፈ ጉባኤው ጀግና ማለት ከእርስ በእርስ ግጭት ወጥቶ በሰላም የሕዝብን ጥያቄ የሚፈታ ነው ብለዋል። መንግሥት በሰላም የሚገቡትን ተንከባክቦ እንደሚቀበል እና እንደሚያቋቁም ተናግረዋል። የሀገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች ልጆቻቸውን እየመከሩ እንዲመልሱ ጠይቀዋል።
በአካባቢው በተፈጠረ ጽንፈኛ ኃይል ስትሰቃዩ መኖር የለባችሁም፣ በቃችሁ ልትሏቸው ይገባል ነው ያሉት። ሰላምን ከጠበቃችሁ የልማት ጥያቄዎቻችሁ ሁሉ ይፈታሉ ብለዋል። የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች በሰላም እና በውይይት እንደሚፈቱም ገልጸዋል።
መሪዎች የሕዝብ ጥያቄ እንዲፈታ በትኩረት እየሠሩ መኾኑን የተናገሩት ምክትል አፈ ጉባኤው ልማታችሁን የሚያቋርጡ ኃይሎችን በቃ ልትሏቸው እና ልትታገሏቸው ይገባል ነው ያሉት።
መንገድ የሚዘጉት፣ ጥሬ እቃ እንዳይገባ የሚያደርጉት፣ ሕዝብን የሚያሰቃዩት፣ ተማሪዎች እንዳይማሩ የሚከለክሉት ከየትም አልመጡም ከእናንተው ውስጥ ናቸው፣ ምከሯቸው እና በሰላም ይግቡ ብለዋል። የልማት ሥራዎች እንዲሠሩ፣ የጠየቋቸው ጥያቄዎች እንዲፈቱ ሰላማቸውን ማረጋገጥ እንደሚገባቸውም አንስተዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን