
ወልድያ: ግንቦት 24/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በቅዱስ ላሊበላ ከተማ ተገኝቶ የተማሪዎቹን ዝግጅት የቃኘው አሚኮ ተማሪዎቹ ከመደበኛ ትምህርታቸው በተጨማሪ የመምህራንን ድጋፍ፣ የቤተመፃሕፍት አጠቃቀምን እና የጋራ ጥናትን በመጠቀም ዝግጅታቸውን እያጠናከሩ መኾናቸውን ተመልክቷል።
በትምህርት ቤቱ ቤተመፃሕፍት ጥናት ላይ እያሉ አሚኮ ያገኛቸው ተማሪ ሳለ አምላክ ታከለ እና አፈወርቅ ማዕረጉ መምህራን በተጨማሪ ሰዓት የመለማመጃ ጥያቄዎችን እና ያለፉ ፈተናዎችን በመስጠት አቅማቸውን እንዲያጎለብቱ እንደረዷቸው ጠቅሰዋል።
ተማሪዎቹ ከመምህራን ድጋፍ በተጨማሪ የራሳቸውን ጥረት እንደሚያደርጉም ነው የገለጹት። የትምህርት ቤቱን ቤተመፃሕፍት እስከ ምሽት ሁለት ሰዓት እንደሚጠቀሙ እና በጋራም እንደሚያጠኑ ተናግረዋል።
ተማሪዎቹ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ እስከ ፈተናው ቀን ድረስ ያለውን ጊዜ በአግባቡ እየተጠቀሙ መኾኑንም አስረድተዋል።
የትምህርት ቤቱ ርእሰ መምህር ኑሩሁሴን ሀሰን በ2017 የትምህርት ዘመን ተማሪዎችን ወደ ዩኒቨርሲቲ ለማሻገር ተጨማሪ የትምህርት ድጋፍ፣ የቤተመፃሕፍት አደረጃጀት እና አጠቃቀም እንዲኹም የሥነ ልቦና ምክር አገልግሎት ድጋፍ እየተደረገ መኾኑን ገልጸዋል።
የላሊበላ ከተማ አሥተዳደር ትምህርት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ዲያቆን ፍቅረየሱስ ሙሉጌታ በ2017 የትምህርት ዘመን 615 ተማሪዎችን ለዩኒቨርሲቲ መግቢያ እንደሚያስፈትኑ ተናግረዋል።
በአካባቢው ባለው የሰላም መደፍረስ ምክንያት ተማሪዎች ላይ የሚደርሰውን ሥነልቦናዊ ጫና ለማቃለል ከተማ አሥተዳደሩ በምክር አገልግሎት ድጋፍ እያደረገ መኾኑንም ነው ያስገነዘቡት።
የሰሜን ወሎ ዞን ትምህርት መምሪያ ምክትል ኀላፊ ወንድወሰን አክሊሉ በጸጥታ ችግር ምክንያት የመማር ማስተማር ሂደቱ ሲስተጓጎል እንደቆየ ገልጸዋል።
ይኹን እንጂ ከሀገር ሽማግሌዎች እና ከጸጥታ መዋቅሩ ጋር በመተባበር ቀድመው የጀመሩ ትምህርት ቤቶችን ሰኔ/2017 ዓ.ም ላይ፣ ዘግይተው የጀመሩትን ደግሞ መስከረም/2018 ዓ.ም ላይ ለማስፈተን ቅድመ ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።
በሁለቱም ዙር 4ሺህ 707 ተማሪዎችን ለማስፈተን የኦንላይን ምዝገባ እንደተከናወነ የገለጹት ምክትል ኀላፊው ከወልድያ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ለተማሪዎች የሥነልቦናዊ ዝግጅት ድጋፍ እየተደረገ መኾኑንም አስታውቀዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን