
ወልድያ: ግንቦት 24/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የክልል እና የዞን ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በሰሜን ወሎ ዞን ከአንጎት ወረዳ ሕዝብ ጋር በአሁንተገኝ ከተማ ሕዝባዊ ውይይት አካሂደዋል።
የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) ሰላም የሚጸናው ሕዝብን አግኝቶ በመምከር እና የሕዝብን ሀሳብ ወደ ተግባር በመፈፀም ነው። ለዚህም ሕዝብ የሰላም ወታደር መኾን ሲችል ነው ብለዋል።
ክልሉ ባለፉት 20 ወራት የገጠመውን ችግር በማረቅ አኹን ላይ ሰላምን የማጽናት እና የልማት ሥራን የማጠናከር ሥራ እየሠራ እንደሚገኝም አስረድተዋል።
ይህ ማለት ችግሩ ሙሉ በሙሉ ተቀርፏል ማለት አይደለም ያሉት ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) ሕዝቡ የደረሰበት መከራ እንዳይደገም ከልብ ስለሰላም መምከር እና መሥራት አለበት ነው ያሉት።
የክልሉ መንግሥት ሕዝብ የሚጠይቀውን ሰላም ይከበርልኝ ጥያቄ ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ በሀገር መከላከያ ሠራዊት እና በክልሉ የጸጥታ ኀይል አቅም ለመመለስ እየሠራ እንደሚገኝም ነው የተናገሩት። ይሁን እንጂ የተገኘው ሰላም ሙሉ በሙሉ ስኬታማ የሚኾነው ሕዝቡም የሰላም ወታደር ሲኾን ነው ብለዋል።
የአንጎት ወረዳ ሕዝብ ከአሁን በፊት ያደርገው የነበረን ሽፍታን የመመከት ተግባር አስቀጥሎ ጽንፈኛን የመዋጋት ሚናውን እንዲወጣም አሳስበዋል።
የሕዝብ ጥያቄ ተሻጋሪ በመኾኑ መንግሥት ኀላፊነቱን በሚገባ እንዲወጣ ሕዝብ ያለውን ባሕላዊ እና ሃይማኖታዊ አደረጃጀቶች ተጠቅሞ ልጆቹን ከመምከር ጀምሮ ሁሉንም የሰላም አማራጭ እንዲጠቀም ነው የጠየቁት።
በውይይቱ የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ የአደረጃጀት ዘርፍ ኀላፊ ፍስሀ ደሳለኝ፣ የሰሜን ወሎ ዞን አሥተዳዳሪ አራጌ ይመር እና የሰሜን ምሥራቅ እዝ ምክትል አዛዥ ሜጄር ጄኔራል ሻምበል ፈረደ ተገኝተዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን