
ባሕር ዳር: ግንቦት 24/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር አካባቢ ርጥበት አጠር እንዲሁም ድርቅ በተደጋጋሚ የሚጎዳው በመኾኑ ያሉትን ጸጋዎች በመጠቀም ዘርፈ ብዙ የግብርና ውጤቶችን በማምረት በምግብ ራስን ከመቻል ባሻገር ለሌሎች ክልሎችም መትረፍ መቻሉ ተገልጿል።
የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ግብርና መምሪያ ኀላፊ አዲሱ ወንዴ በተያዘው የመኽር ወቅት 120 ሺህ 638 ሄክታር መሬትን በማረስ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት እየተሠራ ነው ብለዋል።
4 ሺህ 700 ሄክታር መሬትን በኩታ ገጠም ለማረስ ታቅዶም እስካሁን 3 ሺህ 711 ሄክታር መሬት ተለይቶ ወደ ሥራ ተገብቷል ነው ያሉት።
አምስት ዋና ዋና የሰብል ዓይነቶች በኩታ ገጠም ይለማሉ ያሉት መምሪያ ኀላፊው እነርሱም ማሽላ፣ ጤፍ፣ ስንዴ፣ ዕንቁ ዳጉሳ እና ማሾ ናቸው።
ከግብዓት አኳያ ለ2017/18 የመኽር ምርት 50 ሺህ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለማቅረብ መታቀዱን መምሪያ ኀላፊው ተናግረዋል። ከዚህ ውስጥም 32 ሺህ ኩንታል ማዳበሪያ ወደ ብሔረሰብ አሥተዳደሩ ገብቷል ብለዋል። 12 ሺህ 30 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሮች መሰራጨቱንም አብራርተዋል።
መምሪያ ኀላፊው አያይዘውም 18 ሺህ 90 ኩንታል የከረመ ማዳበሪያ መኖሩንም ጠቁመዋል።
ግብዓትን፣ ቴክኖሎጂን እና በኩታ ገጠም አርሶ የማምረትን ሳይንሳዊ ዘዴዎች አርሶ አደሮች ባሕል እያደረጓቸው ይገኛሉ ያሉት ኀላፊው የአቅርቦት እንዲሁም የአጠቃቀም መሻሻሎች በመኖራቸው ከታቀደው በላይ ምርት ለማግኘት እየተሠራ ይገኛል ብለዋል።
በብሔረሰብ አሥተዳደሩ የግብርና መምሪያ የኤክስቴንሽን ኮሙኒኬሽን ቡድን መሪ አሰፋ ወርቁ በበኩላቸው አካባቢው በዝናብ እጥረት እና በተደጋጋሚ ድርቅ የሚጎዳ በመኾኑ ያሉትን ጸጋዎች በመጠቀም ከ437 ሺህ በላይ ኩንታል የአትክልት ምርት ከመስኖ ልማት ተገኝቷል ነው ያሉት። ምርቱም ከአካባቢው አልፎ ወደ አዲስ አበባ እና ሌሎች አካባቢዎች መላኩን ተናግረዋል።
በሁለተኛው ዙር የመስኖ ልማትም 300 ሺህ ኩንታል የሰብል ምርት መገኘቱን ነው ቡድን መሪው የገለጹት።
የውኃ መሳቢያ ሞተሮችን በመጠቀም ሽንኩርትን እና ቲማቲምን በኩታ ገጠም እርሻ የማምረት ልምዱ ጥሩ መኾኑንም ነው አቶ አሰፋ የገለጹት።
የዋግ ኽምራ ቀጣና በሰፊው ዝናብ አጠር በመኾኑ ከሰብል ምርት ባለፈ አርሶ አደሩ የአበርገሌ ፍየልን በማርባት ተጨማሪ የምግብ ዋስትና መረጋገጫ ኾኖታል ነው ያሉት።
የተከዜ ሰው ሠራሽ ግድብን በመጠቀምም በዓመት እስከ 9 ሺህ 660 ኩንታል ዓሣ እየተመረተ መኾኑን አቶ አሰፋ ተናግረዋል።
ዘጋቢ፦ ሙሉጌታ ሙጨ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
