
ፍኖተሰላም: ግንቦት 24/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በምዕራብ ጎጃም ዞን ደንበጫ ከተማ አሥተዳደር ከ13 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ በኅብረተሰቡ ተሳትፎ እና በመንግሥት በጀት የተገነቡ የልማት ሥራዎች ለአገልግሎት ክፍት ኾነዋል።
የረጅም ጊዜ የማኅበረሰቡ ጥያቄ የነበሩ የድልድይ፣ የውስጥ ለውስጥ መንገድ ጥገና፣ የቢሮ ጥገና እና የዲች ግንባታ ተጠናቅቀው ተመርቀዋል።
ሌላው በጸጥታ ችግር ምክንያት መስከረም 24/2017 ዓ.ም የወደመው የከተማ አሥተዳደሩ ቢሮ ጥገና ተደርጎለት ለአገልግሎት ክፍት ኾኗል።
በከተማ አሥተዳደሩ የተገነቡ የመሠረተ ልማት ሥራዎች 6 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ የተደረገባቸው ናቸው።
በጸጥታው ችግር ምክንያት የወደመውን የከተማ አሥተዳደር ቢሮ ለመጠገን ከ6 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ መደረጉ ተገልጿል ።
ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት የኾኑ የልማት ሥራዎች የማኅበረሰቡ 70 በመቶ ተሳትፎ ያለባቸው ስለመኾናቸው ነው የተነሳው።
በልማት ሥራዎቹ ምረቃ ላይ የተገኙት የደምበጫ ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከተንቲባ ሙሉቀን መኮነን በጸጥታ ችግሩ ምክንያት በርካታ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ውድመቶች ተከስተዋል ብለዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የምዕራብ ጎጃም ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አባይ አለሙ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሰላም አማራጭን ገፍተው ወደ ግጭት የገቡ ኀይሎች ብዙ መሰዋዕትነት አስከፍለዋል ብለዋል።
ግጭቱም ማኅበረሰቡን ከሁለንተናዊ እንቅስቃሴዎች እንዲገታ ማድረጉን ነው የተናገሩት።
የጸጥታ መዋቅሩ ከማኅበረሰቡ ጋር በመቀናጀት በአካባቢው ሰላም እንዲሰፍን እና የልማት ሥራዎች እንዲሠሩ መደረጉንም አንስተዋል።
የጸረ ሰላም ኀይሎች ባደረሱት ጥፋት የደረሰውን ውድመት በመጠገን ሰላም እንዲሰፍን በርካታ ጥረቶች መደረጋቸውን የገለጹት ደግሞ የአማራ ክልል ሥራ አመራር ኢንስቲትዩት አማካሪ ይትባረክ አወቀ ናቸው።
የታጠቁ ኀይሎች የአካባቢውን ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ከመግታት ባለፈ የሚመጣ መፍትሔ ባለመኖሩ አሁንም ማኅበረሰቡ ታጣቂዎች ወደ ሰላም እንዲመለሱ ግፊት ማድረግ አለበት ብለዋል።
ከተማ አሥተዳደሩ ወደ ነበረ ሰላሙ እንዲመለስ የክልሉ መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራም አቶ ይትባረክ ገልጸዋል።
በምረቃ መርሐግብሩ ላይ የክልል፣ የዞን እና የከተማ አሥተዳደሩ መሪዎች እንዲኹም የከተማዋ ነዋሪዎች ተገኝተዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን