ሕዝብ ለድህነት እንዳይጋለጥ ሰላምን አስከብሮ ማልማት ይገባል።

30

ደብረ ታቦር: ግንቦት 24/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ከታች ጋይንት ወረዳ ነዋሪዎች ጋር እየተወያዩ ነው።

ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በደቡብ ጎንደር ዞን ታች ጋይንት ወረዳ በአርብ ገበያ ከተማ ከሕዝብ ጋር እየተወያዩ ይገኛሉ።

በውይይቱ የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ፣ የአማራ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ አማረ ሰጤ፣ የአማራ ክልል ሚሊሻ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አስቻለ አላምሬ፣ የደቡብ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ጥላሁን ደጀኔ፣ የ303ኛ ኮር አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል ተሾመ ይመርን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።

ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎቹ ታች ጋይንት ወረዳ አርብ ገበያ ከተማ ሲደርሱ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።

የታች ጋይንት ወረዳ አሥተዳዳሪ ማንደፍሮ ገበየሁ የወረዳው ሕዝብ ላደረገው ደማቅ አቀባበል ምሥጋና አቅርበዋል። አካባቢው በርካታ ጸጋዎችን ያቀፈ፣ ታሪካዊ ሥፍራዎች ያሉት፣ የመልማት ጸጋ ያለው ነው ብለዋል።

በአካባቢው በተፈጠረው የጸጥታ ችግር በርካታ ጉዳት መድረሱንም ተናግረዋል። የሀገር መከላከያ ሠራዊት እና የክልሉ የጸጥታ ኃይሎች በሠሩት ሥራ አካባቢው ወደ አንጻራዊ ሰላም መመለሱን ነው የገለጹት። የተጀመረውን ሰላም ከሕዝብ ጋር በመኾን ለማስቀጠል እንደሚሠሩም ገልጸዋል።

የደቡብ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ጥላሁን ደጀኔ ጋይንት የጀግና ልጆች መፈጠሪያ፣ ሀገር አደጋ በገጠማት ጊዜ ከፊት የሚሰለፉ ልጆች የሚወጡበት፣ በኢትዮጵያዊነት የማይደራደሩ ልጆች የሚፈልቁባት እንደኾነችም አስረድተዋል።

ጋይንት ለኢትዮጵያ መጽናት አስተዋጽኦ ያደረጉ ጀግኖች ሲበቅሉባት የኖረች አካባቢ ናት ያሉት አሥተዳዳሪው የቀደመውን ጀግንነት አስጠብቃችሁ፣ ጽንፈኝነትን ተከላክላችሁ ሰላምን ማጽናት አለባችሁ ብለዋል።

አሁን ያለው ሰላም የመጣው በነዋሪዎቹ አስተዋጽኦ እንደኾነም ነው የተናገሩት። ከጽንፈኛ አመለካከት ራስን በማራቅ፣ ሰላምን በማስከበር ለልማት መሰለፍ እንደሚገባም አብራርተዋል። ሰላምን ለማደፍረስ የሚነሱ ኃይሎችን መምከር እንደሚገባም ገልጸዋል።

ሰላም ከሌለ ሁሉም የለም ያሉት አሥተዳዳሪው ሰላም ሲኖር ልማት፣ ዕድገት እና የጸና ሀገር ይኖራል ነው ያሉት። ጽንፈኛ ኃይሎች ሕዝብን ሲጎዱ መቆየታቸውንም ገልጸዋል። ሰላምን ማጽናት ለነገ የማይባል ተግባር መኾኑንም አመላክተዋል።

ሰላም ሳይኖር በመቆየቱ ተማሪዎች አልተማሩም፣ አርሶ አደሮች በሰላም ማልማት አልቻሉም፣ ይህን ለመቅረፍ መሥራት ይጠበቃል ነው ያሉት። ሕዝብ ለድህነት እንዳይጋለጥ ሰላምን አስከብሮ ማልማት ይጠበቃል ብለዋል።

ጽንፈኝነት ጥላቻ እና ኀላቀርነት የፈጠረው ለሕዝብ የማይጠቅም አስተሳሰብ መኾኑንም አንስተዋል።

በርካታ የታጠቁ ኃይሎች የሰላም አማራጭን እየተቀበሉ መኾናቸውን የተናገሩት አሥተዳዳሪው አሁንም በጫካ የሚገኙ ታጣቂዎች የሰላም አማራጭን መጠቀም አለባቸው ነው ያሉት።

በይቅርታ የተመሠረተ አብሮነት ድል መኾኑንም ገልጸዋል። ታጣቂዎች ሰላማዊ አማራጭን እንዲጠቀሙ የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች እንዲመክሩም ጠይቀዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous article“በአረንጓዴ አሻራ አረንጓዴ መሬት”
Next articleበደንበጫ ከተማ አሥተዳደር ተገንብተው የተጠናቀቁ የልማት ሥራዎች ለአገልግሎት ክፍት ኾኑ።