“በአረንጓዴ አሻራ አረንጓዴ መሬት”

14

ባሕር ዳር: ግንቦት 22/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአርሶ አደር ልጅ ነኝ፤ ወላጆቼ እና መሰል የቀያችን ማኀበረሰብ ውኃ የሚቀዳው ከመኖሪያ ቤቱ በቅርብ ርቀት ላይ ከሚገኘው ልባ ወንዝ ነው። ወንዙን ተከትሎም በየቦታው የሚፈስ ምንጭ አለ።

ልባ ወንዝ በሰሜን ጎጃም ዞን ባሕር ዳር ዙሪያ ወረዳ የሚገኝ ሲኾን ለዓባይ ገባር ወንዝ ነው።

ዓመት እስከ ዓመት ካፍ እስከ ገደፉ ጢም ብሎ የሚገማሸረው የልባ ወንዝን በመጠቀም የአካባቢው ማኀበረሰብ የጓሮ አትክልት በሰፊው ያለማል። ፍራፍሬ እያመረተም ከራሱ ባሻገር ለገበያ ያቀርባል። አካባቢው በጋ እና ክረምት የሰብል ምርት ይታፈስበታል ብል የተጋነነ እንዳይመስላችሁ።

የልባ ወንዝን ተከትሎ የሚገኙ ሸለቆዎች፣ ተራራዎች እና ጉድባዎች ሰርክ አረንጓዴ ናቸው። ዛፉ ቅጠሉን እያረገፈ እንደገና ያለመልማል። ጥቁር አፈሩ ሁሌ እንደረሰረሰ እና በቶካ ሳር እንደተሸፈነ ይከርማል።

“እንዳማሩ አይዘልቁ” እንዲሉ ታዲያ ልባ ወንዝ ከዓመት ዓመት መጠኑ እየቀነሰ መምጣት ማኀበረሰቡን ሳያሳስበው አልቀረም። ይባስ ብሎ ዓመቱን ሙሉ ይወርዱ የነበሩት እነዚያ ሕይዎት አድን እና የበረሃ ገነት የነበሩት ምንጮችም አቅማቸው ተዳከመ።

ኀብረተሰቡ አትክልት እና ፍራፍሬ ማምረት ቀርቶ ጉሮሮን የሚያርስበት ውኃ ከልባ ወንዝ ማግኘት የሰማይ ያህል ራቀው። ስለኾነም በጠፍ ጨረቃ እና በጠራራ ፀሐይ ረጅም ጎዳና እየተጓዙ ውኃ ከዓባይ ወንዝ መቅዳት የተለመደ ኾነ።

በቃ! የክረምቱ ወራት ወጥቶ በጋው ሲብት ” ትንሽ ትልቁ፤ ሴት እና ወንዱ” በመጨነቅ ወደ ፈጣሪ ያማትራሉ።

የኀብረተሰቡን ምሬት በአንክሮ የተመለከተው መንግሥት እጁን አጣጥፎ አልተቀመጠም። ጥልቅ ጉድጓድ ቆፍሮ ንጹሕ መጠጥ ውኃ እንካችሁ አላቸው። ይህም ቢኾን ግን አንጀት አርስ መኾን አልቻለም።

የዛሬ አምስት ዓመት ገደማም የግብርና ሙያተኞች ኀብረተሰቡን ሰብስበው “ለምን የልባ ወንዝ ቀነሰ፤ ምንጮችስ ስለምን ይደርቃሉ?” ሲሉ እንዲመክሩበት እንዳደረጉም አስታውሳለሁ።

በምክክሩ ለልባ ወንዝ መቀነስ እና ለልባ ምንጮች መድረቅ ምክንያቱ ያ የጠጠር መጣያ ያልነበረው ደን እየተመነጠረ በረሃማነት እየተስፋፋ መምጣቱ እንደኾነ ድምዳሜ ላይ ተደረሰ። መፍትሔውም ሁሉም ሰው የተራቆተውን አካባቢ ችግኝ ለመትከል፣ ለመንከባከብ እና ለመጠበቅ ተስማማ፤ የተባለውም ተተገበረ።

“የመከረ ተጠቀመ” እንዲሉ በውስን ዓመታት ውስጥ ተስፋ ሰጭ ውጤት ታዩ። ተራቁተው የነበሩ አካባቢዎች አገገሙ፤ ምድረ በዳ የመሰሉት ተራሮች አረንጓዴ ሸማ ተጎናጸፉ።

የውኃው ነገርስ? ማኀበረሰቡ ውኃ ከልባ ወንዝ እና ወንዙን ተከትለው የነበሩት ምንጮች መልሰው ማመንጨት በመጀመራቸው በአቅራቢያው በፈለገው ሰዓት ውኃ ቀድቶ ጠጣ።

በ2011 ዓ.ም የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ እንደ ሰሜን ጎጃም ሁሉ በሌሎች አካባቢዎችም ትሩፋቱን ይዞ መምጣቱን እኔ ታዝቤያለሁ።

ሁለተኛውን አብነት ልጥቀስ መገኛው አዊ ብሔረሰብ አሥተዳድር ነው፤ ልዩ ቦታው ዝህሪ ተራራ ይባላል። የዚህ አካባቢ ከአረንጓዴ አሻራ በፊት ተራራው የተራቆተ ነበር። በዚህም በርካቶች በቁጭት ከንፈራቸውን እንዲነክሱ አድርጓቸዋል።

ምስጋና ለአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ይድረሰውና ኀብረተሰቡ በየዓመቱ ሰኔ ግም ሲል በዘመቻ እየወጣ ችግኝ እንዲተክልበት ተደረገ፤ ተንከባከቡትም። ሥፍራው በመጠበቁም የተተከለው ችግኝ ጸደቀ።

ዛሬ ላይ ዙሪያ ገባው በደን የተሸፈነ ነው። በመኾኑም የተራራው ግርጌ ክረምት ከበጋ ምንጭ የሚወርድበት አካባቢ ኾኗል።

ሌላው ማንሳት የፈለኩት በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የጣቁሳ አካባቢ አርሶ አደሮች ችግኝን በወል ተክለው መንከባከብ የሁል ጊዜ ሥራቸው ካደረጉ ሰነባበቱ። ይህን የተቀደሰ ተግባር ወጥ አድርገውም አዝልቀውታል። መላ ሕዝቡ የደኑ ዘብ ኾነ ማለት ይቻላል።

ዛፍ ያለ አግባብ መቁረጥ በጣቁሳ ማኀበረሰብ ዘንድ ነውር ነው። ይልቁንም አርሶ አደሮች በየጎጡ ችግኝ መትከልን ባሕል ያደረጉት ሁሉ ይመስላል። በዚህ ሰናይ ምግባራቸውም የተራቆተን መሬት እንዲያገግም አድርገዋል።

የተዳከሙ ምንጮችን አጎልብተዋል። እየጠፉ የነበሩ አዕዋፋት እና እንስሳትን መልሰዋቸዋል። በዚህም ንብ አንቢዎች ከሌላው ጊዜ በተሻላ መልኩ ተጠቃሚ መኾን እንደቻሉም ታዝበናል።

በሌሎች የክልሉ አካባቢዎችም መሰል የአረንጓዴ ዓሻራ በረከት መኖሩ ሳይታለም የተፈታ ነው። ድሮስ ሕዝብ ካበረ “ተራራ ይገፋል” መባሉ ለዚህም አይደል።

በአንጻሩ ግን ችግኝን በዘመቻ እየወጡ በወል መትከሉ ጥሩ ነው። ውጤትም ተገኝቶበታል። ነገር ግን አንዳንድ አካባቢዎች ባለፉት ጊዜያት ለተከላ ወጥተው ጭቃ እንዳይነካቸው ሲጨነቁም ታዝቤያለሁ።

መንግሥት ውድ የሥራ ሰዓትን ዘግቶ እና ባለጉዳይን በር ላይ አቁሞ “ችግኝ ልትከል” ብሎ የወጣ ሲቭል ሰርቫንት ቄንጠኛ ፎቶ ለመነሳት ሲሯሯጥ አይቼም አፍሬበታለሁ። ይህን ሳነሳ በድፍረት ያለመሸማቀቅ ነው።

መሥሪያ ቤቶችን በተመለከተም “አምና የተከልሁት ችግኝ የት ደረሰ?” ብለው መጠየቅን እና ራሳቸውን መፈተሽ ይኖርባቸዋል። አንዳንዶቹ ተቋማትማ ለተከታታይ ዓመት በአንድ ተመሳሳይ ቦታ ላይ ችግኝ ሲተክሉ የቱ ጸደቀ የቱስ ደረቀ ብለው አዙረው ማየት ግድ ይላቸዋል ብየ አስባለሁ።

መሰል የለበጣ የችግኝ ተከላ ከሚዘወተርባቸው ቦታዎች አንዱ የባሕር ዳሩ የቤዛዊት ተራራ እና አካባቢው መኾኑን ለማስታወስ ነው። በሌሎች አካባቢዎችም መሰል መስተካከል የሚኖርበት ድርጊት ስለመኖሩ በማመን እንማርበት ለማለት ነው።

በመጨረሻም በየዓመቱ ለችግኝ ተከላ እንደምንረባረበው ሁሉ እንክብካቤው ላይም መትጋትን መልመድ ይኖርብናል ባይ ነኝ።

መገናኛ ብዙኃንም “ተተከለ ከማለት በዘለለ ጸደቀን አጠናክረን መዘገብ ይኖርብናል እላለሁ።

ባለፈው ዓመት በአረንጓዴ ዓሻራ መርሐ ግብር 1 ነጥብ 375 ቢሊዮን ችግኝ ተተክሏል። 86 በመቶ የሚኾኑት ችግኞችን ውኃ የማጠጣት፣ የማረም፣ የመኮትክት እና ጥላ የማልበስ ሥራም ተሠርቷል። በዚያም መሠረት አምና ከተተኩት ችግኞች ውስጥ 82 በመቶ የሚኾነው እንደጸደቀ ከክልሉ ግብርና ቢሮ የተገኘው መረጃ ያሳያል።

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ለ2017/18 የአረንጓዴ ዓሻራ መርሐ ግብር ከ1 ነጥብ 6 ቢሊዮን በላይ ችግኝ ለመትከል አቅዶ እየሠራ መኾኑን ከሰሞኑ ማስታወቁን ልብ ይሏል።

“በአረንጓዴ አሻራ አረንጓዴ መሬት” ለመፍጠር 207 ሺህ ሄክታር መሬት ለተከላ ተዘጋጅቷል። 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ጉድጓድ ለማዘጋጀት ታስቦ እስካሁን 200 ሚሊዮን ጉድጓድ ተቆፍሯል። ቀሪ የተከላ ጉድጓዶችም በቀጣይ ቀናት እንደሚከናወኑ ተገልጿል።

ሰላም!

ዘጋቢ: ሙሉጌታ ሙጨ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous article✍የኢትዮጵያ የከፍታ ዘመን!
Next articleሕዝብ ለድህነት እንዳይጋለጥ ሰላምን አስከብሮ ማልማት ይገባል።