✍የኢትዮጵያ የከፍታ ዘመን!

20

✍የኢትዮጵያ የከፍታ ዘመን!

ባሕር ዳር: ግንቦት 24/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያውያን የከፍታ ዘመን ተደርጎ ይነገራል የአጼ ካሌብ ዘመን። አጼ ካሌብ የታዜና ልጅ ሲኾኑ ከ417 እስከ 527 ዓ.ም የኖሩ እንደኾኑ ነው ታሪካቸው የሚያስረዳው።

ንጉሱ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ከፍ ያለ ስም እና ተግባር ያከናወኑ መሪም ናቸው። በአጼ ካሌብ ዘመን ኢትዮጵያ ከፍ ያለ ብልጽግና እና ሥልጣኔ ላይ የደረሰች ቢኾንም ይህን ሥልጣኔ ያልወደዱት ሀገራት ጦር ይሰብቁባት ስለነበር ከጦርነት መላቀቅ አልቻለችም።

ሀገሪቱን በውስጥም ኾነ በውጭ ሊጎትቷት እና ሊጥሏት የሚፈልጉ በርካቶች ነበሩ። ንጉሱ ቀይባሕርን ለመቆጣጠር እና የሀገራቸውን ጥቅም ለማስጠበቅ ከቀይ ባሕር እስከየመን የዘረጉት መንግሥታቸው የሀገሪቱን ከፍታ አስጠብቋል።

ንጉሱ ቀይ ባሕርን እና አካባቢውን ለመቆጣጠር መርከብ ያስፈልጋቸው ስለነበር አዶሊስ በተባለ ቦታ ላይ የመርከብ ማሠሪያ አሠርተው እንደነበር ታሪካቸው ያትታል።

ንጉሱ በወቅቱ የምስማር መስሪያ የሚኾን የብረት ማዕድን ሀገራቸው ላይ ባለመመረቱ ከሌሎች ሀገሮች በተለየ መርከቦቹን የሚሠሩት በገመድ ነበር ይህም ኾኖ መርከቦቹ ሮማውያን ከሚሠሩት መርከቦች መጠናቸው እኩል ነበሩ።

ንጉሱ የሀገሪቱን ጥቅም ለማስጠበቅም 230 ያክል መርከቦችን በቀይ ባሕር ቀጣና አሠማርተው እንደነበርም የባዛታይን የታሪክ ጸሐፊዎች ከትበዋል።

የንጉሱ በዚህ አካባቢ የተሰማራው 70ሺህ ጦር እንደነበር ነው የሚነገረው። በዚህ ጊዜ የኢትዮጵያ ስም እና ብልጽግናዋም ከፍ ያለ ነበር።

✍የሞባይል ስልክ አጀማመር በኢትዮጵያ!

በዓለም አቀፍ ደረጃ የ121 ዓመታት ታሪክ ያለው የሞባይል ስልክ በኢትዮጵያ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ ግንቦት 19 ቀን 2017 ዓ.ም 34 ዓመቱን አስቆጥሯል። በወቅቱ የሞባይል ስልክ አገልግሎት ብርቅ ስለነበር ብዙዎች ለመመዝገብ ፍላጎቱ ነበራቸው።

የኢትዮ ቴሌኮም መረጃ እንደ ሚያስረዳው ዶክተር ልኡልሰገድ ዓለማየሁ እና አቶ ወንድወሰን ደምረው ግንቦት 19 ቀን 1991 ዓ.ም ሞባይል ስልክ ከወሰዱ የመጀመሪያዎቹ ተጠቃሚዎች መካከል ነበሩ። ሲሞቹን ለመውሰድ ረጃጅም ሰልፎችም ነበሩ።

የሞባይል ቀፎዎቹም እንደዛሬው ሳይኾን ለመያዝ ከበድ የሚል ስለነበር ለአያያዝ አስቸጋሪ ነበሩ።

የዛሬ 18 ዓመት አንድ ሰው የሞባይል ባለቤት ለመኾን 2ሺህ 600 ብር መክፈል እና እንደ ንግድ ፈቃድ ወይም የቤት ካርታ ማሟላት ይጠበቅበት ነበር። ዛሬ ግን መታወቂያ በማሳየት እና 15 ብር በመክፈል ብቻ የሞባይል ስልክ አገልግሎት ማግኘት ይችላል።

በመጀመሪያዎቹ ዓመታት እጅግ ጥቂት የነበሩት የሞባይል ስልክ ተጠቃሚዎች ዛሬ በኢትዮጵያ ቁጥራቸው 56 ሚሊዮን ደርሷል። በቀጣይ ጥቂት ዓመታት ውስጥ ይህንን ቁጥር ወደ 103 ሚሊዮን ለማድረስ ድርጅቱ እየሠራ ስለመኾኑም ካስቀመጠው መረጃ ለመረዳት ይቻላል። ለዚህም የቴሌኮም መሠረተ ልማት ማስፋፊያ ሥራዎች በስፋት እየተከናወኑም ይገኛሉ።

✍ገመድ አልባ ቴሌግራፊ!

የቴሌኮሙኒኬሽን ታሪክ ጸሐፊዎች እንደሚሉት የሽቦ አልባ ቴሌግራፊ ፈጠራ በታሪክ ማህደር የዚህ ሳምንት ውጤት ነው። ፈጠራውን የአንድ ሰው ነው ብሎ መውሰድ ግን አይቻልም። የበርካታ ሳይንቲስቶች እና መሐንዲሶች የጋራ ጥረት ውጤት ነው።

እንደ ጎርጎሳውያን ዘመን በ1896 በዚህ ሳምንት የጣሊያን መሐንዲስ ጉግሊየልሞ ማርኮኒ በዩናይትድ ኪንግደም ለሽቦ አልባ ቴሌግራፊ የመጀመሪያውን የፈጠራ ባለቤትነት አግኝቷል።

የሽቦ አልባ የመገናኛ ዘዴዎች በከባቢ አየር ንብረቶች ተጽዕኖ ስር ስለሚወድቁ እንደ ኤሌክትሪክ ፍሳሾች እና አይወናይዜሽን ያሉ ነገሮች ሞገዶችን በማስተጓጎል የመገናኛ ችግር ይፈጥራሉ።

ይህንን ችግር ለመቅረፍ የስትራስቡርግ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር ፈርዲናንድ ብራውን መሬትን እና ውኃን እንደ ሞገድ መሪ የሚጠቀም ድብልቅ የሥርዓት ሀሳብ አቅርበዋል። ይህ ጽንሰ-ሀሳብ ሞገዶች እንደ ፍሪኩዌንሲያቸው በልዩነት ወደ ምድር ውስጥ ዘልቀው መግባት እንደሚችሉ ይገልጻል።

ብራውን ይህንን ንድፈ ሐሳብ በመጠቀም ያከናወናቸው ሙከራዎች አስደናቂ ውጤት አስገኝተዋል።

በመጀመሪያ የሬዲዮ ሞገዶችን ያገኘው ሄርትዝ የተባለ ሰው ሲኾን ከዚያም የሄርትዝ ሞገዶችን በመጠቀም ምልክቶችን ያለሽቦ ያስተላለፈው ማርኮኒ የፈጠራው ቁልፍ ሰው ተብሎ ይወሳል።

ይኹን እንጂ፣ እንደ ሞርስ፣ ፖፖቭ፣ ሰር ደብሊው ፕሪስ፣ ሎጅ እና በተለይም ብራንሊ የመሳሰሉ ምሁራን ለስርጭቱ አስፈላጊ የኾኑ መሳሪያዎችን በማዘጋጀት ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከታቸው ነው የሚነገረው።

የፍልስፍና ባለሙያው ቮልቴር እንደተናገረው፣ “ሳይንስ ከጊዜ ወደ ጊዜ ግላዊ ከመኾን እየወጣ መጥቷል እናም ዕድገት ሁልጊዜ ማለት ይቻላል የብዙ ሰዎች የጋራ ጥረት ውጤት ነው” የሚለው ሀሳብ፣ የሽቦ አልባ ቴሌግራፊን ጨምሮ ለብዙ ዘመናዊ ፈጠራዎችም ይሠራል።

ዘጋቢ:- ምሥጋናው ብርሃኔ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየአማራ ክልል ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴዎች የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደርን የሥራ አፈጻጸም ገመገሙ።
Next article“በአረንጓዴ አሻራ አረንጓዴ መሬት”