
ጎንደር: ግንቦት 23/2017 ዓ.ም (አሚኮ) አማራ ኤፍ ኤም ጎንደር 105 ነጥብ 1 ራዲዮ ጣቢያ የተመሰረተበትን አራተኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ከአድማጮች ጋር ቆይታ አድርጓል። ሃሳባቸውን በስልክ ያጋሩን አቶ ጋሻው የኑስ ከአለፋ ከጣቢያው መመሥረት ጊዜ ጀምሮ አብሮነታቸው እንዳልተለየ አስታውሰዋል። አስተማሪ እና አዝናኝ መረጃዎችን ከጣቢያው እንዳገኙ በመግለጽ ጣቢያው ዐይን እና ጆሮ ኾኖ አገልግሎናል ብለዋል።
ተቋሙ ለሰላም መረጋገጥ የበኩሉን ኀላፊነት እየተወጣ ነው ያሉት ሌላው አድማጭ አቶ ታመነ ተሻገር ከታች አርማጭሆ የሕዝብ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ የድርሻውን ሲወጣ ቆይቷልም ብለዋል። ይህንንም አጠናክሮ በመቀጠል በቀጣይ ተደራሽነቱን በማስፋት ጥራት ላይ ሊሠራ እንደሚገባም ነው የተናገሩት።
የአድማጭ ተመልካቹን ፍላጎት መሠረት በማድረግ ሥራዎችን ለመከወን ዝግጁ ነን ያለው ጋዜጠኛ አገኘሁ አበባው ሥራን በትጋት በመፈጸም ተቋሙ ያስቀመጠውን ግብ ለማሳካት በትኩረት እየሠራን ነው ብሏል።
“ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን” በሚል መርህ የሕዝብ ዐይን እና ጆሮ ኾነው በማገልገላቸው ኩራት እንደሚሰማው የተናገረው ጋዜጠኛ ያየህ ፈንቴ በክልሉ ሰላም እንዲሰፍን፣ ሕዝቡ የልማት ተጠቃሚ እንዲኾን እና መልካም አስተዳደር እንዲረጋገጥ የተሠሩ ሥራዎች አበረታች እንደነበሩ ተናግረዋል።
የአማራ ኤፍ ኤም ጎንደር 105 ነጥብ 1 ራዲዮ ጣቢያ ዋና አዘጋጅ እመቤት ሁነኛው ተቋሙ አዳዲስ ይዘቶችን በመቅረጽ እና ማሻሻያዎችን በማድረግ ለሕዝብ ተደራሽ መኾን መቻሉን ተናግረዋል።
ከአራት ዓመት በፊት በራዲዮ ስርጭት ሥራውን የጀመረው ተቋሙ ከጥር ወር 2017 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ የቴሌቪዥን ስቱዲዮ በጎንደር ከተማ በመገንባት የሚዲያውን ተደራሽነት የማስፋት ሥራ መሠራቱን ተናግረዋል።
በቀጣይ ተደራሽነቱን በማስፋት የአካባቢው ብሎም የክልሉ ሰላም እንዲረጋገጥ እንሰራለን ያሉት ዋና አዘጋጇ የአካባቢውን የቱሪዝም እና ምጣኔ ሃበታዊ አቅም በማስተዋወቅ ለሕዝብ ተጠቃሚነት እንሰራለን ብለዋል።
ሕዝብ የሚያነሳቸው የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ ሚዲያው የድርሻውን ይወጣልም ብለዋል።
ዘጋቢ:- ዳንኤል ወርቄ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን