
ወልድያ: ግንቦት 23/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የክልል እና የዞን ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በደቡብ ወሎ ዞን ከደላንታ ወረዳ እና ከወገልጤና ከተማ አሥተዳደር ከተውጣጡ የማኅበረሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት አካሂደዋል።
ውይይቱን የመሩት የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) በሀገር ደረጃ ሰላም እንዲኖር ማኅበረሰብ ትውፊቶቹን ጠብቆ ሊኖር ይገባዋል ብለዋል። ለምን የአባቶቻችንን መስመር ሳትን? ለምን እሴቶቻችንን አጣን ? ብለን ጠይቀን መፍትሄ ስናፈልቅ የችግራችንን ምንጭ እናደርቃለን ብለዋል ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ። በመንግሥት እና በሕዝብ መካከል የተፈጠሩ የግንኙነት እና የቁርኝት ችግሮችን መርምረን መፍትሄ ማፍለቅ ይኖርብናልም ብለዋል።
ደላንታ ወረዳ በተፈጥሮ ሀብት እና በማኅበራዊ እሴት የበለፀገ ነው ያሉት ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ እሴቶቹ ግን በሂደት ተሸርሽረዋል ብለዋል። ስለዚህ ለምን እና እንዴት ብለን መምከር ይገባል፣ በዚህ ላይ መምከር ካልቻልን ማኅበረሰብ እንደ ማኅበረሰብ አይቀጥልም ብለዋል።
መክረን መልስ ማግኘት ከቻልን እና ራሳችንን የመፍትሄ ምንጭ ኾነን ከሠራን ሁለንተናዊ ሀብታችንን ተጠቅመን ራሳችንን እናበለፅጋለን ሲሉ አስረድተዋል።
በመኾኑም የችግሩ ምንጭ፣ የችግሩ መፍትሄም ደላንታዊ ነው፣ በችግሩ እና በመፍትሄው ላይ ልንመክር ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን