
ደብረ ታቦር: ግንቦት 23/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በጉብኝቱ የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ፣ የአማራ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ አማረ ሰጤ፣ የአማራ ክልል ሥራ አመራር ኢንስቲትዩት ፕሬዝዳንት እሱባለው መሰለ፣ የደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ደሴ መኮንን እና ሌሎች የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎቹ የቤጌ ምድር የባሕል ማዕከል፣ የደብረ ታቦር መብራት ሰብስቴሽን፣ የደብረ ታቦር ሪጂናል ላቦላቶሪ እና የደብረ ታቦር አዳሪ ትምህርትን የግንባታ ሂደት ነው የጎበኙት።
የደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ደሴ መኮንን በከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች የተጎበኙት ፕሮጄክቶች ለከተማዋ እድገት ትልቅ አስተዋጽኦ ያላቸው ናቸው ብለዋል።
የደብረ ታቦር ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት በ1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር እንደሚገነባ ተናግረዋል። ግንባታው በጥሩ ሂደት ላይ መኾኑንም ገልጸዋል። በተያዘለት ጊዜ መጠናቀቅ እንደሚችል የግንባታ ሂደቱ ያሳያል ነው ያሉት። ግንባታው በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ ከተማ አሥተዳደሩ ድጋፍ እና ክትትል እንደሚያደርግም ገልጸዋል።
በከተማዋ እየተገነባ የሚገኘው የመብራት ሰብስቴሽንም በመጠናቀቅ ላይ መኾኑን ተናግረዋል። 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር የተመደበለት ፕሮጄክት መኾኑንም አንስተዋል። ለኢንቨስትመንት ፍሰት ማነቆ ኾኖ የቆዬውን የኀይል አቅርቦት ችግር የሚፈታ መኾኑን ተናግረዋል።
የመብራት ኀይል ሰብስቴሽኑ ለከተማዋ ብቻ ሳይኾን እስከ 130 ኪሎሜትር ርቀት ለሚገኙ አካባቢዎችም አገልግሎት የሚሰጥ መኾኑን ገልጸዋል። ከዚህ በኋላ በደብረ ታቦር እና አካባቢው የኀይል አቅርቦት ችግር እንደማይኖርም ተናግረዋል። ባለሀብቶች የኀይል አቅርቦት ችግር ሊፈጠር እንደማይችል በመረዳት ወደ ከተማዋ መጥተው ኢንቨስት እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል። የከተማዋ አሥተዳደር እና የከተማዋ ሕዝብ በመብራት ሰብስቴሽን ግንባታው ደስተኞች መኾናቸውንም አንስተዋል።
በደብረ ታቦር ከተማ እየተገነባ የሚገኘው የቤጌምድር የባሕል ማዕከል ግንባታም በከተማዋ እየተገነቡ ከሚገኙ ትልልቅ ፕሮጄክቶች መካከል አንደኛው መኾኑን ነው የተናገሩት። ነገር ግን ፕሮጄክቱ በተያዘለት ጊዜ አለመጠናቀቁን ነው የገለጹት። የባሕል ማዕከሉ ግንባታን የክልሉ ከፍተኛ መሪዎች ማየታቸው ጥሩ አጋጣሚ መኾኑን የተናገሩት ከንቲባው ያለበትን ችግር ማስረዳታቸውን እና በሚጠናቀቅበት አግባብ መነጋገራቸውን አመላክተዋል።
የባሕል ማዕከሉ የጎንደር በጌምድር ባሕል እና እሴት የሚገለጽበት ትልቅ ፕሮጄክት መኾኑን ነው ያነሱት። የባሕል ማዕከሉን በፍጥነት ለማጠናቀቅ የመሪዎችን እና የሕዝቡን ጥረት እንደሚጠይቅም ገልጸዋል።
በከተማዋ እየተገነቡ የሚገኙ ሌሎች የልማት ሥራዎችን ለማጠናቀቅ ሥራዎች እየተሠሩ መኾናቸውንም ተናግረዋል። ከተማዋ በመነቃቃት ላይ የነበረች ነገር ግን የሰላም እጦቱ የጎዳት ከተማ ናት ብለዋል። የጸጥታ ችግሩ ባለሀብቶች ከከተማዋ እንዲወጡ አድርጓቸው መቆየቱን ነው የገለጹት። አሁን ላይ ከተማዋ ወደ ሰላም መመለሷን እና የልማት ሥራዎችም እየተነቃቁ መኾናቸውን ተናግረዋል።
ባለሀብቶችም በተሟላ ሁኔታ ወደ ልማት እንዲገቡ እየተሠራ ነው ብለዋል። የተጀመሩ እና ቃል ተገብተው ያልተጀመሩ ሥራዎች እንዲሠሩ ጥረት እየተደረገ መኾኑንም አንስተዋል። አሁን ያለው ሰላም ለከተማዋ ልማት ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ነው የተናገሩት።
ማኅበረሰቡ የልማት ሥራዎች እንዲሠሩ ትልቅ እገዛ እያደረገ መኾኑን ገልጸዋል። እያደረገ ያለውን ተሳትፎ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል። የከተማዋን ልማት ለማረጋገጥ የማኅበረሰብ ተሳትፎ የማይተካ ሚና አለው ነው ያሉት።
የልማት እድሎችን በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባም አመላክተዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን