የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተናን ለመውሰድ በእውቀት እና በስነ ልቦና ዝግጁ መኾናቸውን ተማሪዎች ተናገሩ።

12

ደባርቅ: ግንቦት 23/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተናን የሚወስዱ ተማሪዎች በስነ ልቦና እና በእውቀት ዝግጁ እንዲኾኑ ለማስቻል የተለያዩ የአቅም ግንባታ ሥራዎችን ሲሠራ መቆየቱን የሰሜን ጎንደር ዞን ትምህርት መምሪያ ገልጿል፡፡

በዞኑ ሰባት ወረዳዎች በሚገኙ 19 የመሰናዶ ትምህርት ቤቶች ከአምስት ሺህ በላይ የሚኾኑ ተማሪዎች የዘንድሮ ዓመት የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ይወስዳሉ ተብሎ ይገመታል፡፡ የሰሜን ጎንደር ዞን ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ክቡር አሰፋ ከመደበኛ የትምህርት ጊዜው በተጨማሪ ቅዳሜ እና እሁድን ጨምሮ በተለያዩ ጊዜያት በተመረጡ መምህራን የማጠናከሪያ ትምህርት ሲሰጥ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡
የአዳር ጥናት መርሐ ግብር በማዘጋጀት ተማሪዎችን ለማገዝ ጥረት ማድረጉንም አንስተዋል፡፡

አቶ ክቡር አክለውም ከደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር የተሻለ ውጤት ያላቸውን ተማሪዎች በልዩነት የማገዝ ሥራ ተሠርቷል ብለዋል፡፡
የደባርቅ ከተማ ትምህርት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ፈረደ ይትባረክ በበኩላቸው በከተማ አሥተዳደሩ በሚገኙ ሶስት የመሰናዶ ትምህርት ቤቶች 670 ተማሪዎች የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መግቢያ ፈተናውን እንደሚወስዱ ገልጸዋል፡፡
በትምህርት ቤት ውስጥ የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ይገኛሉ፤ ስለኾነም በትምህርት ቤቶች ከሚገኙ የልዩ ፍላጎት ዩኒቶች ጋር በመተባበር የልዩ ፍላጎት ተማሪዎችን የማገዝ ሥራ ሲሠራ መቆየቱንም ተናግረዋል፡፡
ከሥርዓተ ፆታ ክበባት አስተባባሪዎች ጋር በመተባበርም ለሴት ተማሪዎች የተለያዩ ድጋፎች ሲደረጉ መቆየታቸውን አብራርተዋል፡፡

የደባርቅ ከተማ አሥተዳደር የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ጉድኝት ሱፐርቫይዘር ሰለሞን አማረ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ዙሪያ ተማሪዎችን የማወያየት እና ችግሮችን የመለየት ሥራ መከናወኑን አንስተዋል፡፡
ከዚህ በፊት በነበረው የፈተና ሂደት ተማሪዎች ውጤታቸው ዝቅ ያለበትን የትምህርት አይነት በመምረጥ የማብቃት ሥራ መሠራቱን አብራርተዋል።

ተማሪዎችም በበኩላቸው ለፈተና ብቁ እንዲኾኑ የሚያስችላቸውን የተለያየ ትምህርት እና ሥልጠና ሲወስዱ መቆየታቸውን ገልጸዋል፡፡
ከትምህርት ድጋፉ በተጨማሪ በማኅበራዊ እና በስነ ልቦና ብቁ እንዲኾኑ የሚያስችሉ የተለያዩ ሥልጠናዎች መሰጠታቸውን ተናግረዋል፡፡
ስለኾነም ፈተናውን ለመውሰድ የተሻለ የስነ ልቦና እና የእውቀት ዝግጅት ማድረጋቸውን አብራርተዋል፡፡

በቀሪ ጊዜያትም ተማሪዎች ሳይዘናጉ እስከ ፈተና ጊዜው ድረስ እንዲዘጋጁ ለማድረግ የክትትል ሥራው ይቀጥላል ተብሏል፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleከፍተኛ መሪዎች በወገልጤና ከተማ ከነዋሪዎች ጋር እየተወያዩ ነው።
Next articleየደሴ ሙዚየም እድሳትና ጥገና ተደርጎለት ዳግም አገልግሎት መሰጠት ጀመረ።