ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃን ለማጣራት እየተሠራ መኾኑን የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን አስታወቀ።

12

ሁመራ: ግንቦት 22/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የፌዴራል መንግሥት ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃን ለመቆጣጠር ያጸደቀውን የመንግሥት ሠራተኞች አዋጅ ተግባራዊ ለማድረግ እንቅስቃሴ መጀመሩን የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን አስታውቋል። በዞኑ የተሟላ ስብዕና ያለዉ ሲቭል ሰርቪስ በመገንባት የተቋማትን ዕቅድ አፈጻጸም ለማሳደግ እና የኅብረተሰቡን እርካታ ማረጋገጥ ይቻል ዘንድ ባሳለፍነው ሚያዝያ ወር በመንግሥት አገልግሎት እና አሥተዳደር ሪፎርም ዙሪያ ለመሪዎች እና ለመንግሥት ሠራተኛው የግንዛቤ ፈጠራ መሰጠቱ ይታወሳል።

ይሄንን ተከትሎ የአፈጻጸም አቅጣጫ በማስቀመጥ ተግባራዊ ለማድረግ እንቅስቃሴ መጀመሩን የዞኑ አሥተዳዳሪ አሸተ ደምለው ተናግረዋል። ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ፍትሐዊ ተወዳዳሪነትን እየጎዳ በመኾኑ መሪዎች ትኩረት ሰጥተው ሊሠሩበት እንደሚገባም ነው ያሳሰቡት። የትምህርት ማስረጃን የማጣራት ሂደቱ ከመሪዎች የሚጀምር በመኾኑ በሙያ እና በብቃት ልክ የሚኖርባት ሀገር መፍጠር ያስችላል ነው ያሉት።

የትምህርት ማስረጃ የማጣራት ሂደቱ ለአሚኮ ማብራሪያ የሰጡት የዞኑ ሲቪል ሰርቪስ መምሪያ ኀላፊ ዘሪሁን ነጋ እያንዳንዱ ሠራተኛ ማስረጃውን በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ ለሚመለከተው አካል ማቅረብ ይጠበቅበታል ብለዋል። ከወረዳ እስከ ዞን ድረስ በሚመለከታቸው አካላት የሚሰበሰበው ማስረጃ ትክክለኛነቱ የሚረጋገጠው በትምህርት ሚኒስቴር እና በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መኾኑንም ገልጸዋል።

ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃን ለመቆጣጠር የጸደቀው አዲሱ የመንግሥት ሠራተኞች አዋጅ ቁጥር 1353/2017 አግባብነት የሌለው የትምህርት ማስረጃ ይዞ የተገኘ አካል በሥራ መደቡ ላይ መቀጠል እንደማይችል መደንገጉንም አስረድተዋል።

ዘጋቢ፦ አምሳሉ አሞኘ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleበትምህርት ዘርፉ ያሉ ችግሮችን በጥናት እና ምርምር መፍታት ከትምህርት ተቋማት ይጠበቃል።
Next articleከፍተኛ መሪዎች በወገልጤና ከተማ ከነዋሪዎች ጋር እየተወያዩ ነው።