
ባሕር ዳር: ግንቦት 22/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የዝንጀሮ ፈንጣጣ በሽታ (Mpox) “ክሌድ 1” እና “ክሌድ 1ቢ” በሚባሉ ሁለት ዋና ዋና የቫይረስ ዝርያዎች አማካይነት ሲሰራጭ እንደቆየ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የተገኘው መረጃ ያመላክታል። “ክሌድ 1” የሚባለው የቫይረሱ ዓይነት በማዕከላዊ አፍሪካ በስፋት የሚገኝ ሲኾን፣ ክሌድ 1B” እየተስፋፋ ያለ እና በጣም አደገኛ መኾኑ ይነገራል።
በፈረንጆቹ 2022 ቀለል ያለው እና በምዕራብ አፍሪካ የሚገኘው “ክሌድ 2” የተባለው የበሽታው ዝርያ በዓለም ዙሪያ በወረርሽኝ መልክ ተከስቶ እንደነበር መረጃዎች ያመላክታሉ። በወቅቱ በሽታው ቫይረሱ ተከስቶባቸው የማያውቁት የአውሮፓ እና የእስያ ሀገራትን ጨምሮ 100 በሚጠጉ ሀገራት ውስጥ ተከስቶ ነገር ግን ለበሽታው ተጋላጭ የኾኑ ሰዎችን በመከተብ ወረርሽኙ በቁጥጥር ስር ውሏል።
የበሽታው ምልክቶች መጀመሪያ የሚታዩት ትኩሳት፣ ራስ ምታት፣ እብጠት፣ ጀርባ ህመም እና የጡንቻ ህመምን ያካትታል። ትኩሳት ከተከሰተ በኋላ ከፊት ጀምሮ ቀሪውን የሰውነት ክፍልን የሚያዳርስ ሽፍታ የሚከሰት ሲኾን፣ በአብዛኛው በእጅ መዳፍ እና በእግር መረገጫ ላይ ይከሰታል። በሰውነት ላይ የሚያጋጥመው ሽፍታ በጣም የሚያሳክክ እና የሚቆጠቁጥ ሲኾን፣ በተለያዩ የለውጥ ደረጃዎች ውስጥ አልፎ በመጨረሻም እብጠት በመፍጠር ኋላ ላይም የሚከስም ነው። ቁስለቱም ጠባሳን ትቶ ሊያልፍ ይችላል።
በሽታው በአብዛኛው ከሁለት እስከ ሦስት ሳምንት ባለው ጊዜ ውስጥ በራሱ የሚጠፋ ይኾናል። በበሽታው የተያዘው ሰው በጣም የተጎዳ ከኾነ፣ ቁስለቱ አጠቃላይ ሰውነቱን፣ በተለይ አፍ፣ ዓይን እና የመራቢያ አካላት ላይ ከባድ ጉዳት ሊያደርስም ይችላል። የበሽታው ከሰው ወደ ሰው የመተላለፊያ መንገድ :-
በሽታው ቤተ ሙከራ ውስጥ በሚደረግ ምርመራ የሚገኝ ቫይረስ ሲኾን፣ በሰውነት ንክኪ ይተላለፋል። የዝንጀሮ ፈንጣጣ ወሲባዊ ግንኙነትን፣ የቆዳ ንክኪን እና በቅርብ ርቀት ላይ ኾኖ ማውራትን ወይም መተንፈስን ጨምሮ በበሽታው ከተያዙ ሰዎች ጋር በሚኖር የቀረበ ግንኙነት ከሰው ወደ ሰው ይተላለፋል።
የበሽታው ቫይረስ ወደ ሰውነት በቆሰለ ቆዳ፣ በመተንፈሻ አካላት፣ በዓይን፣ በአፍንጫ ወይም በአፍ በኩል ሊገባ ይችላል።
በቫይረሱ የተበከሉ የመኝታ አልባሳት፣ በልብሶች እና በፎጣዎች አማካይነት በሚኖር ንክኪም በሽታው ሊተላለፍ ይችላል። ቫይረሱ ካለባቸው ዝንጀሮዎች እና አይጦችን ከመሳሳሉ ጋር የሚኖር ንክኪም ሌላው የበሽታው መተላለፊያ መንገድ ነው። ከሁለት ዓመት በፊት የዝንጀሮ ፈንጣጣ በዓለም ዙሪያ በበርካታ ሀገራት ውስጥ በተከሰተበት ጊዜ ቫይረሱ በዋናነት በወሲባዊ ግንኙነት በሚፈጠር ንክኪ አማካይነት ነበር የተሠራጨው።
ባለፈው ዓመትም በዲሞክራቲክ ኮንጎ ውስጥ የተከሰተው የበሽታው ወረርሽኝ የተስፋፋው በወሲባዊ ግንኙነት በሚፈጠር ንክኪ ሲሆን፣ ነገር ግን በሌሎችም አካባቢዎች ተመሳሳይ ቫይረስ ሊገኝ ችሏል። መከላከያ እና ህክምናውን በተመለከተም የዝንጀሮ ፈንጣጣን ለማከም የተዘጋጀ ህክምና የታመሙ ሰዎችን ለማዳን በጣም ጠቃሚ ቢኾንም፣ ነገር ግን ህክምናው ምን ያክል ውጤታማ እንደኾነ የሚያሳይ ውስን ጥናት እንዳለ ነው የሚገለጸው።
የዝንጀሮ ፈንጣጣ ወረርሽኝን፣ በሽታውን በመከላከል መቆጣጠር የሚቻል ሲኾን፣ ይህንንም ለማድረግ ተመራጩ መንገድ የመከላከያ ክትባት መስጠት ነው። በአኹኑ ጊዜ ሦስት በሽታውን መከላከያ የክትባት ዓይነቶች ቢኖሩም፣ ክትባቶቹ የሚሰጡት ለበሽታው ተጋላጭ ለኾኑ እና በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር የቀረበ ንክኪ ላላቸው ብቻ ነው።
ይኹንና ያሉት የክትባት ዓይነቶች አዲስ ከተከሰተው የበሽታው ዝርያ አንጻር ምን ያህል የመከላከል አቅም አላቸው የሚለውን ለማወቅ ተጨማሪ ሙከራዎች ማድረግ ስለሚያስፈልግ፣ የዓለም ጤና ድርጅት ሁሉም ሰው መከተብ አለበት ብሎ አይመክርም። ባለፈው ዓመትም የአፍሪካ ኅብረት ለኮቪድ ተመድቦ ከነበረ ገንዘብ ላይ 10 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዶላር ለሲዲሲ በመስጠት የዝንጀሮ ፈንጣጣን ለመቆጣጠር የሚደረገውን ጥረት መደገፉን የቢቢሲ ዘገባ አመላክቷል።
የአፍሪካ ሲዲሲ እንደሚለው ካለፈው ዓመት ጥር መጀመሪያ አንስቶ እስከ ሐምሌ መጨረሻ ድረስ ባሉት ሰባት ወራት ውስጥ ከ14 ሺህ 500 በላይ በዝንጀሮ ፈንጣጣ የተያዙ ሰዎች የተመዘገቡ ሲኾን፣ ከ450 በላይ ሰዎች ደግሞ በበሽታው ሕይወታቸው አልፏል። የበሽታው ክስተት 96 በመቶው በዲሞክራቲክ ኮንጎ ውስጥ የተመዘገበ ሲኾን፣ ጎረቤት ወደኾኑት እና የዝንጀሮ ፈንጣጣ እምብዛም ወደ ማይታወቅባቸው ቡሩንዲ፣ ኬንያ፣ ሩዋንዳ እና ኡጋንዳ ተስፋፍቶ እንደነበርም ይታወሳል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን