
ደሴ: ግንቦት 22/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የጣና ሐይቅና ሌሎች የውኃ አካላት ጥበቃና ልማት ኤጀንሲ የአማራ ክልል ደንና አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ተጠሪ ተቋም ነው። ኤጀንሲው የውኃ አካላትን ከጉዳት የመጠበቅ፣ ብዝኀ ሕይወትን ጠብቆ እንዲለሙ የማድረግ፣ የውኃ አካላትን ከመጤ አረም የመጠበቅ እና ቀድሞ የመከላከል እንዲኹም የውኃ አካላት ተፋሰሶችን ከብክለት የመጠበቅ አላማዎችን ይዞ ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል።
ተቋሙ የተቋቋመበትን ተግባር እና ኀላፊነት ለባለድርሻ አካላት ግንዛቤ ለመፍጠር የሚያስችል የውይይት መድረክ በኮምቦልቻ ከተማ እያካሄደ ነው። በደቡብ ወሎ ዞን የወረባቦ እና የአልብኮ ወረዳ ተወካይ የኾኑት አደም አሕመድ እና ለይላ ሠይድ ለአሚኮ እንደገለጹት ኤጀንሲው በየአካባቢያቸው ያሉትን ሐይቆች ከመጠበቅ አንጻር ጉልህ ሚና መጫወት እንደሚኖርበት አመላክተዋል።
የደቡብ ወሎ ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ አሊ ይማም በዞኑ አራት ሐይቆች መኖራቸውን አስታውሰው ሐይቆቹን ከማልማት እና ከመጠበቅ አንጻር ሥራዎች እየተሠሩ ቢኾንም በይበልጥ አመርቂ ሥራ ለመሥራት ግን ኤጀንሲው ጋር በትብብር መሥራት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል። የጣና ሐይቅና ሌሎች የውኃ አካላት ጥበቃና ልማት ኤጀንሲ አማካሪ ማግኘት መልካሙ እንደገለጹት ኤጀንሲው ባለፉት 5 ዓመታት በጣና ሐይቅ ላይ ተከስቶ የነበረውን የእንቦጭ አረም ከመከላከል ጀምሮ የተለያዩ ሥራዎችን ሲሠራ ቆይቷል።
አኹን ላይ በተለያዩ የክልሉ ከተሞች የውኃ አካላትን በመጠበቅ በኩል ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ የሚያስችል የውይይት መድረክ እየተዘጋጀ መኾኑን የጠቆሙት አማካሪው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር በጋራ ለመሥራትም መታቀዱን አስረድተዋል።
ዘጋቢ:- ሕይወት አስማማው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን