“ከጦርነት አዙሪት መውጣት ያልቻልነው መሠረታዊ ችግሮቻችን ላይ ተመካክረን መፍትሄ ማምጣት ባለመቻላችን ነው” ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ

55

አዲስ አበባ: ግንቦት 22/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የፌዴራል ተቋማት እና ማኅበራት የአጀንዳ ማሠባሠብ የምክክር መድረክን እያካሄደ ነው። የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ የነፃነት ተምሳሌት፣ ለዓለም የሥልጣኔ መነሻ፣ የበርካታ ቋንቋዎች እና ባሕሎች ሕያው ሙዚየም ናት ብለዋል።

ይኹን እንጂ እነዚህን እሴቶች የሚፈታተኑ መሠረታዊ እና ሀገራዊ የኾኑ ጎልተው የሚታዩ አለመግባባቶች ጦር አማዘው ለዘመናት ዋጋ አስከፍለውናል ነው ያሉት። ኮሚሽነሩ አክለውም ለዘመናት የተሻገረውን የኢትዮጵያን ሕዝብ የዘመናት ቋጠሮ ለመፍታት ኮሚሽኑ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር እየሠራ መኾኑንም አንስተዋል።

ለውጤታማነቱም መንግሥት እና የሚመለከታቸው አካላት የትግራይ ክልል በምክክር ሂደቱ ተሳታፊ እንዲኾን ምቹ ኹኔታ እንዲፈጠር፣ የታጠቁ አካላት ወደ ምክክር እንዲመጡ ጥረት እንዲደረግ፣ በማረሚያ ቤት እና በስደት ያሉ ዜጎች የሕግ የበላይነትን ባከበረ መልኩ እንዲካተቱ እንዲደረግ ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ጥሪ አቅርበዋል።

በመድረኩ የ38 ተቋማት ተወካዮች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የክልል ምክር ቤት ተወካዮች፣ የጸጥታ እና የፍትሕ አካላት እንዲኹም ልዩ ልዩ ባለድርሻ አካላትም ተሳታፊ ናቸው። ዛሬ የተጀመረው የፌዴራል ተቋማት እና ማኅበራት የአጀንዳ ማሠባሠብ መድረክ ለተከታታይ ሦስት ቀናት የሚቀጥል ይኾናል።

ዘጋቢ፦ ቤተልሄም ሰለሞን

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleሥጋ ደዌ በሽታ በባክቴሪያ እንጅ በዘርም አይተላለፍም፤ እርግማንም አይደለም።
Next articleየጣና ሐይቅና ሌሎች የውኃ አካላት ጥበቃና ልማት ኤጀንሲ የውኃ አካላትን የመጠበቅ ተግባሩን እንዲወጣ ተጠየቀ።