ምርት እና ምርታማነትን ለማሳደግ እየሠራ መኾኑን የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር አስታወቀ።

14

ከሚሴ: ግንቦት 21/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የ2017/18 የመኸር ሰብል ልማት የዘር ጅማሮ በአማራ ክልል ኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር በሁሉም አካባቢዎች እየተካሄደ ነው። በደዋ ጨፋ ወረዳ የጎበያ ቀበሌ አርሶ አደሮች በዝናብ እጥረት ምክንያት ዘግይተው ዘር መጀመራቸውን ገልጸው ከባለፈው ዓመት የተሻለ ምርት ለማምረት አቅደው ሥራ መጀመራቸውን ተናግረዋል።

በመኸር እርሻ ሥራቸው የምርት ማሳደጊያ ግብዓት እና ቴክኖሎጂ ተጠቅመው ከባለፈው ዓመት የተሻለ ለማምረት አቅደው ሥራ መጀመራቸውን ገልጸዋል። የደዋ ጨፋ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ እንድሪስ መሐመድ በወረዳው ምርታማነትን ለማሳደግ ኩታገጠምን መሰረት ያደረገ ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል።

በወረዳው በመኸር ምርት ዘመኑ የተያዘው እቅድ እንዲሳካም በቂ የባለሙያ ድጋፍ እና ክትትል እየተደረገ መኾኑን ጠቅሰዋል። የደዋ ጨፋ ወረዳ ዋና አሥተዳዳሪ መሐመድ ጌታቸው በወረዳው ከሄክታር የሚገኘውን ምርት ለማሳደግ አርሶ አደሮች ሙሉ ፓኬጅን ተጠቅመው እንዲሠሩ በሁሉም ቀበሌዎች ድጋፍ እና ክትትል እንደሚደረግ አስረድተዋል።

የግብርና ሥራው የጸጥታ ችግር እንዳይገጥመው እና አርሶ አደሮች ተረጋግቶ ሥራውን እንዲሠራ በቀጠናው የሕግ ማስከበር ሥራ መሠራቱን አስረድተዋል። የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ግብርና መምሪያ ምክትል ኀላፊ ሀሰን ሰይድ በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ከ58 ሺህ በላይ ሄክታር መሬት በዘር በመሸፈን ከ1 ነጥብ 7 ሚሊዮን በላይ ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሠራ መኾኑን ጠቁመዋል።

በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ከ50 ሺህ በላይ ሰው ሠራሽ ማዳበሪያ ለማቅረብ ታቅዶ እስካሁን 40 ሺህ ኩንታል የሚኾን ማዳበሪያ ቀርቦ ለአርሶ አደሮች እየተሰራጨ ነው ብለዋል።

ዘጋቢ:- ይማም ኢብራሒም

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየትምህርት ዘርፉን ማገዝ የልጆችን የወደፊት እጣ ፈንታ ማገዝ ነው።
Next articleየከተማዋን ሰላም ዘላቂ እና አስተማማኝ ለማድረግ እየተሠራ መኾኑን የደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር አስታወቀ።