የትምህርት ዘርፉን ማገዝ የልጆችን የወደፊት እጣ ፈንታ ማገዝ ነው።

30

አዲስ አበባ: ግንቦት 21/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የሰሜኑ ጦርነት ከተከሰተ እስካኹን በትምህርቱ ዘርፍ ሰፊ ጉዳት አጋጥሟል። የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ይፋ ባደረገው መረጃ መሠረት ባለፋት ዓመታት በክልሉ በተካሄደ ግጭት ከ6ሺህ 154 በላይ ትምህርት ቤቶች ጉዳት ደርሶባቸዋል።
ይህ ማለት በክልሉ ከሚገኙ ትምህርት ቤቶች 57 በመቶዎቹ ትምህርት ቤቶች ለጉዳት ተዳርገዋል።

በተያዘው የትምህርት ዘመን ወደ ትምህርት ይመጣሉ ተብሎ ከሚጠበቁ ተማሪዎች ውስጥ ከ4 ነጥብ 1 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎቸ ወደ ትምህርት ቤት አልገቡም። ይህ የኾነው ደግሞ ከ4ሺህ 821 በላይ ትምህርት ቤቶች በግጭቱ ምክንያት ባለመከፈታቸው ነው። በአማራ ክልል በተከሰተው ግጭት የመማማሪያ ቁሳቁሶች ላይ ጉዳት ተከስቷል።

በክልሉ በትምህርት ዘርፍ ያጋጠመውን ጉዳት ለመቀነስ እና የትምህርቱን ዘርፍ ለማነቃቃት የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ከድጋፍ አድራጊ ድርጅቶች ጋር ውይይት ተደርጓል። በዚህ ውይይት ላይ የተገኙት በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ክላስተር አስተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) በክልሉ ያለውን የትምህርት ዘርፍ ለማነቃቃት ድጋፍ አድራጊዎች እገዛ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

በትምህርት ቁሳቁስ አቅርቦት በኩልም ድጋፍ እንዲደረግ ያሳሰቡት ዶክተር ሙሉነሽ ተማሪዎች በቤታቸው ኾነው በዲጂታል በመታገዝ መማር የሚችሉባቸው ኹኔታ እንዲፈጠሩ እገዛ ማድረግ እንደሚገባም አስታውቀዋል። የትምህርት ዘርፉን ማገዝ የልጆችን የወደ ፊት እጣ ፈንታ ማገዝ በመኾኑ የተማሪዎች የትምህርት ጊዜ እንዳይባክን ሁሉም ትብብር ማድረግ ይገባዋል ብለዋል።

የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ድኤታ አየለች እሸቴ በበኩላቸው ግጭቶች የልጆቻችንን የወደፊት እጣ ፈንታ ሊጎዳ አይገባም ብለዋል። ተማሪዎችን እና ትምህርት ቤቶችን ማገዝ የሀገርን መፃኢ ዕድል ማገዝ በመኾኑ መንግሥታዊም ኾኑ መንግሥታዊ ያልኾኑ ተቋማት ትምህርት ቤቶችን በማገዝ እና መልሶ በመገንባት ሊተባበሩ እንደሚገባም አስታውቀዋል።

ዘጋቢ፦ ተመስገን ዳረጎት

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleፋይዳ – ቴክኖሎጂ የወለደው ሀቀኛ መታወቂያ!
Next articleምርት እና ምርታማነትን ለማሳደግ እየሠራ መኾኑን የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር አስታወቀ።