ፋይዳ – ቴክኖሎጂ የወለደው ሀቀኛ መታወቂያ!

33

ባሕር ዳር: ግንቦት 21/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ቴክኖሎጂ እንዲወለድ መነሻ የሚኾነው የሰው ልጅ ችግሮችን ለመፍታት ያለው ጥልቅ ፍላጎት ነው፡፡ ይህ ውልደት ደግሞ የሰውን ልጅ ድካም፣ ጊዜ እና ገንዘብ በመቆጠብ ሕይወትን ቀላል ያደርጋል፡፡ አገልግሎት በመስጠት እና በመቀበል ሂደት ያሉ ክፍተቶችን ለማቃናት ከተጀመሩ ሀገራዊ ሥራዎች ውስጥ አንዱ ፋይዳ ብሔራዊ መታወቂያ ነው፡፡

ፋይዳ ሰዎች ማንነታቸውን ለመግለጽ ሳይቸገሩ አገልግሎት ማግኘት የሚችሉበት፣ በመታወቂያ የሚደረጉ የማጭበርበር ድርጊቶችን ማስቀረት የሚቻልበት፣ የግለሰቦችን የሥነ ሕዝብ መረጃ መጠበቅ የሚቻልበት፣ ኋላ ቀር አሠራሮችን ማዘመን እና ሕይወትን ምቹ እና ቀላል ማድረግ የሚቻልበት ዘመናዊ እና ሀቀኛ መታወቂያ ነው፡፡

የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም የባለድርሻ አካላት ዳይሬክተር የኾኑት ሳሚናስ ሰይፉ ከአሚኮ ዲዲታል ሚዲያ ጋር ባደረጉት የስልክ ቃለ መጠይቅ ፋይዳ የመታወቂያ ፍልስፍናን የቀየረ ዘመናዊ የማንነት ማረጋገጫ መኾኑን ገልጸውልናል። ከዚህ ቀደም መታወቂያ የምንለው በእጅ የምንዳስሰውን የማንነት መለያ ካርድ ነበር፤ በፋይዳ ግን ይህን እሳቤ በቁጥር ቀይሯል ብለዋል።

ዳይሬክተሩ ይህ ቁጥር ዲጂታል ምህዳሩ ላይ የምንገለጽበት ወይም የምንታወቅበት መለያ ቁጥር መኾኑን እና የግለሰቡን ማንነት ማሳየት የሚችሉ ባለ 12 እና ባለ16 አኀዝ ቁጥሮች እንዳሉት አስታውሰዋል፡፡ ሰዎች ፋይዳን ለማግኘት ከብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ከተመዘገቡ በኋላ ቁጥሩ ተልኮላቸውም መታወቂያ አልደረሰኝም ሲሉ እንደሚሰማ ገልጸው ነገር ግን የተላከላቸው ቁጥር በራሱ የእነሱን ማንነት የሚገልጽ መታወቂያ አማራጭ መኾኑን ጠቁመዋል፡፡

ፋይዳ ሰዎች እንደምርጫቸው የመታወቂያ አማራጭ እንዲኖራቸው የሚያስችል መኾኑን ሲገልጹ መታወቂያውን በምን መንገድ ልያዘው የሚለውን ካሰብን አትመን አልያም በስልክ መያዝ እንደሚቻል አስረድተዋል፡፡ የፋይዳ መታወቂያ ሌላኛው እና ትልቁ ጥቅም የመታወቂያውን ትክክለኛነት በፍጥነት ማረጋገጥ የሚቻልበት መንገድ ነው፡፡ ድሮ በምናውቀው የመታወቂያ ሥርዓት የአንድን ሰው ማንነት ለማረጋገጥ መታወቂያውን ከሰጠው ሕጋዊ አካል ጋር ደውለን ካልሆነ በስተቀር በትክክል ለማረጋገጥ አስቸጋሪ ነበር ያሉት አቶ ሳሚናስ በፋይዳ ይህ ችግር በቀላሉ ተወግዷል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በዚህ የዲጂታል ሥርዓት የግለሰቦችን ትክክለኛ ማንነት በሁለት መንገድ ማረጋገጥ የሚያስችል አማራጭ መኖሩን እና መንገዶቹ ደግሞ ያለመረጃ መረብ እና መረጃ መረብን በመጠቀም የሚሠሩ መኾናቸውን ዳይሬክተሩ አስረድተዋል። የታተመውን የፋይዳ መታወቂያ ካርድ የምንጠቀም ከሆነ በካርዱ ላይ ያለውን የማንነት መለያ ምሥጢራዊ ኮድ ቴሌብርን፣ የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራምን እና የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ያዘጋጇቸውን መተግበሪያዎች በመጠቀም መለየት ይቻላል ብለዋል፡፡

በቀጣይ እየተሠራበት ያለው ሌላው የመለያ አማራጭ በታተመው የፋይዳ መታወቂያ ላይ ያለውን መለያ ኮድ እና የባለመታወቂያውን የፊት ገጽ በማንበብ በሁለቱ መካከል መመሳሰል መኖሩን በማመሳከር የሚከናወን አማራጭ እንደሚኖርም ጠቁመዋል፡፡ የተለያዩ ተቋማት የዲጂታል ሥርዓት ሲኖራቸው ከፋይዳ ጋር በማስተሳሰር የተገልጋዮችን የማንነት መረጃ ተገልጋዮች በሚፈቅዱበት የመልዕክት ልውውጥ አማካኝነት የሚረጋገጥበት ደግሞ በመረጃ መረብ የተሳሰረ የማረጋገጫ መንገድ እንደኾነ ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

እንዲህ አይነት የማረጋገጫ ስልት ለተቋማት ሲመቻች የግለሰቦችን መረጃ ተገልጋዮች ከፈቀዱ ብቻ እንጂ ማንኛውም የግል መረጃ ክፍት ተደርጎ የማይተው ነው ብለዋል፡፡ ለምሳሌ የግብር ከፋይ መለያ ቁጥር ለማግኘት አገልግሎት የሚጠይቅ ግለሰብ ለገቢ ተቋማት ካመለከተ በኋላ በፋይዳ ላይ የተመዘገበውን የግለሰቡን መረጃ ለማግኘት ተቋማት ሲጠይቁ ወደ ግለሰቡ በሚላክ የመፍቀጃ መልዕክት ግለሰቡ ማረጋገጥ ይኖርበታል፡፡

አቶ ሳሚናስ አክለውም በጣት አሻራ፣ የታተመውን መታወቂያ በአካል በመስጠት፣ የፋይዳ ቁጥርን አሊያም የፊት ገጽን በማስነበብ (scanning) መረጃችንን ተቋማት እንዲያገኙ መፍቀድ እንችላለን ነው ያሉት፡፡ የፋይዳ መታወቂያ ላይ ያሉ መረጃዎችን የሚፈልጉ ዲጂታል ሥርዓት ያላቸው ተቋማት የግለሰቦችን መረጃ ማግኘት የሚችሉት የመታወቂያው ባለቤት ሊፈቅድ በሚችልበት አማራጭም ቢኾን ሁሉንም ዓይነት መረጃ ሳይኾን እንደ ተቋማቱ ባህርይ የሚያስፈልጋቸውን መረጃ ብቻ የሚጠይቁበት አሠራር እንዳለም ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous article“ሕዝቡ የሚያነሳቸውን የልማትና የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎችን ለመመለስ በትኩረት እየተሠራ ነው” ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)
Next articleየትምህርት ዘርፉን ማገዝ የልጆችን የወደፊት እጣ ፈንታ ማገዝ ነው።