
ወልድያ: ግንቦት 21/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜን ወሎ ዞን ዋድላ ወረዳ በኮን ከተማ ሕዝባዊ ውይይት እየተካሄደ ነው። በውይይቱ የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)፣ የርእሰ መሥተዳድሩ አደረጃጀት አማካሪ ፍስሃ ደሳለኝ፣ የሰሜን ወሎ ዞን አሥተዳዳሪ አራጌ ይመር እና የሰሜን ምሥራቅ ዕዝ ምክትል አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ሻምበል ፈረደ ተገኝተዋል።
የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) የሊቃውንት መፍለቂያ ከሆነው የዋድላ ሕዝብ ጋር ለመመካከር መገኘት ደስታን ይፈጥራል ብለዋል። የዋድላ ወረዳ ሕዝብ የአሥተዳደር እና የአመራር ብልሃትን ከቤተ እምነት መዋቅር ጀምሮ በውል የሚገነዘብ መሆኑንም ገልጸዋል።
በማንኛውም ሁኔታ የመልካም አሥተዳደር እና የልማት ጥያቄዎች ሊነሱ ይችላሉ፤ የመልስ መጓደልም ሊያስቆጣ ይችላል፤ ይሁን እንጂ ጥያቄዎችን ለሰላማዊ የመልስ አማራጭ መጠቀም እንጂ ነፍጥ ማንሳት ይበልጥ አካባቢን ያወድማል ነው ያሉት። በሰላማዊ ንግግር፣ በሽምግልና እና በምርጫ ክርክር መሞገት እንጂ ወደ አውዳሚ ጦርነት መግባት መፍትሔ እንደማያስገኝም ተናግረዋል።
የዋድላ ሕዝብ የአስተውሎትና የጥበብ ባለቤት ነው፤ በዚህ ጥበብም የራሱን ዘላቂ ሰላም ሊጠብቅበት እንደሚገባም አሳስበዋል። የዋድላ ሕዝብ በራሱ አቅም፣ በመከላከያ ሠራዊት እና በክልሉ የጸጥታ መዋቅር ታግዞ ያጋጠመውን የሰላምን ችግር መቅረፍ መቻሉንም አንስተዋል። የተገኘውን ሰላምን ለማፅናት ሕዝብ ከልብ መምከር አለበት ነው ያሉት።
የመንግሥት የሥልጣን ምንጭ በካርድ ነው፤ ቀጣይ የመንግሥት ሥልጣንም የሚገኘው በካርድ መኾኑን ሕዝብ ያውቃል፤ ይህን መሠረት አድርጎ አካባቢውን ከአልባሌ ሁከት መጠበቅ እና ሰላምን ማስፈን ያስፈልጋል ብለዋል።
ሕዝቡ የሚያነሳቸውን የልማትና የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎችን ለመመለስ በትኩረት እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል። የተጀመሩ ልማቶች በፍጥነት እንዲጠናቀቁ፣ ያልተጀመሩት ምክንያታቸውን በማጣራት በፍጥነት ወደ ሥራ እንዲገቡ ይደረጋል ነው ያሉት።
ይህን ለማድረግ ግን ሰላም ያስፈልጋልና ህብረተሰቡ በአንድ እጁ ሰላም በሌላኛው ልማት በመያዝ ለቀጣይ የማኅበረሰብ እድገት እንዲተጋ አደራ ብለዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!