
ባሕር ዳር: ግንቦት 21/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ከ3 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር በላይ በኾነ ወጭ በሰቆጣ፣ በደብረ ታቦር እና በፍኖተ ሰላም ከተሞች አዳሪ ትምህርት ቤቶችን እያስገነባ ይገኛል። ትምህርት ቤቶቹ በሳይንስ፣ በቴክኖሎጅ፣ በሕክምና፣ በመሪነት እና በሌሎች የሙያ ዘርፎች ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ተማሪዎችን ለማፍራት እንዲቻል የታቀዱ ናቸው።
በክልሉ እየተገነቡ ከሚገኙ ሦስት አዳሪ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ደግሞ የሰቆጣ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ግንባታ ለአካባቢው የሚኖረውን ፋይዳ እና ያለበትን ደረጃ እንካቹሁ ብለናል። የትምህርት ቤቱ ተቆጣጣሪ መሀንዲስ እንዬው እውነቱ ግንባታውን በሁለት ዓመት ለማጠናቀቅ ታስቦ የካቲት 2016 ዓ.ም ወደ ሥራ መገባቱን አስታውሰዋል።
በክልሉ መንግሥት 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ተመድቦለት እንደነበርም ተናግረዋል። ግንባታው በሁለት ተቋራጮች ተከፍሎ በመከናወን ላይ እንደኾነም ገልጸዋል። አሁን ላይ አንደኛው የግንባታ ምዕራፍ (ሎት አንድ) 65 በመቶ፣ ሁለተኛው ምዕራፍ (ሎት ሁለት) ደግሞ 35 በመቶ፣ በአጠቃላይ የግንባታ ሂደቱ ደግሞ 50 በመቶ መድረሱን መሐንዲሱ ተናግረዋል።
ከዚህ በፊት በክልሉ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት ግብዓት በወቅቱ ለማቅረብ አስቸጋሪ እንደነበር ያነሱት ተቆጣጣሪ መሐንዲሱ አሁን ላይ በተፈጠረው አንጻራዊ ሰላም ፕሮጀክቱን በጥራት እና ከተቀመጠለት ጊዜ ቀድሞ ለማጠናቀቅ በትኩረት እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል። ተቆጣጣሪ መሐንዲሱ እንዳሉት ግንባታው በ16 ሄክታር መሬት ላይ የሚያርፍ ነው። በውስጡ የሴት እና የወንድ ተማሪዎች ማደሪያ ክፍሎች፣ የመማሪያ ክፍሎች፣ ቤተ መጽሐፍት፣ የአሥተዳደር ግንባታዎች፣ የእግር፣ የቅርጫት፣ ቮሊቦል እና የእጅ ኳስ ሜዳዳዎችን የያዘ ነው ብለዋል።
ከዚህም በተጨማሪ አትክልት እና የተለያዩ አቅርቦቶች የሚከማችበት የራሱ ስቶር፣ ካፍቴሪያ፣ የተማሪዎች የውበት ሳሎን እና ሱቆች እና ክሊኒክ የመሳሰሉ መገልገያዎችን ግንባታው ያካተተ ነው። ተገንብቶ ሲጠናቀቅ 600 ተማሪዎችን ማስተናገድ ይችላል ነው የተባለው። የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ምክትል ኀላፊ ፍታለሽ ምህረቴ ትምህርት ቤቱ በተቀመጠለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ በየጊዜው ድጋፍ እየተደረገ መኾኑን ገልጸዋል።
ትምህርት ቤቱ በክልል አቀፍ ደረጃ በሚሰጠው የ8ኛ ክፍል ፈተና የተሻለ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎችን ተቀብሎ የሚያስተናግድ ነው ብለዋል። ከብሔረሰብ አሥተዳደሩ ባለፈ በክልሉ ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎችን ጭምር እንደሚቀበልም ገልጸዋል። ይህም ተማሪዎች ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን ከመቀላቀላቸው በፊት የተሻለ ትምህርት እንዲያገኙ እና በሥነ ልቦናም እንዲዘጋጁ ያግዛል ነው ያሉት። በተለይም ደግሞ አካባቢው በተፈጥሮ እና ሰው ሠራሽ አደጋዎች ተጋላጭ በመኾኑ በኢኮኖሚ ችግር ምክንያት ወደ ሌላ ቦታ ተጉዘው መማር የማይችሉ ተማሪዎች በተመቻቸ ሁኔታ እንዲማሩ አቅም የሚፈጥር ነው ብለዋል።
ይህም የምጣኔ ሃብትን እና ማኅበራዊ ችግርን ይቀርፋል ነው ያሉት ምክትል መምሪያ ኀላፊዋ። በአካባቢው የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎችም የተለያዩ የግብይት ሥርዓቶችን በማቋቋም ተጠቃሚ ሊያደርግ የሚችል መኾኑን አንስተዋል።
ዘጋቢ: ዳግማዊ ተሠራ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን