
ጎንደር: ግንቦት 20/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የጎንደር ዩኒቨርሲቲ “ታሪክን እያወሳን፣ አንባቢን እያነሳሳን የዩኒቨርሲቲያችንን የዕውቀት ጉዞ እናከብራለን” በሚል መሪ መልዕክት የመጽሐፍት ዓውደ ርዕይና ባዛር እያካሄደ ነው። በመርሐ ግብሩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የጎንደር ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት አሥራት አጸደወይን (ዶ.ር) ኢትዮጵያ የዘመናት የትምህርት እና የሥነ ጽሑፍ ተግባራት የመከወን ታሪክ ያላት መኾኗን አንስተዋል።
የኢትዮጵያውያን ደራሲያን ተቋማዊ ድጋፍ ባለማግኘታቸው እና በፈተና ውስጥ ሆነው በመሥራታቸው እንደ ሀገር አመርቂ ውጤት ማስመዝገብ እንዳልተቻለ ነው ያስታወቁት። በርካታ ደራሲያን በራሳቸው ጥረትና ትጋት በድርሰቱ ዓለም ጎልተው በመውጣት ለወጣት ደራሲያን አርዓያ መኾን እንደቻሉም ተናግረዋል።
ሥነ ጽሑፍ እና ንባብን የሚያበረታቱ፣ የኪነ ጥበብ ቡድኖችን የሚያጀግኑ፣ በከተሞች የመጽሐፍትን አውደ ርዕይ በማዘጋጀት፣ የጥበብ ሰዎችን የሚያበረታቱ ተግባራትን ማስቀጠልና በሀገር ውስጥ ቋንቋ የተጻፉ መጽሐፍትን በውጭ ቋንቋ በመተርጎም የጥበብ ሥራችን እንዲያድግ የሚመለከተው ሁሉ ሊሠራ ይገባል ነው ያሉት።
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ያካሄደውን የመጽሐፍት አውደ ርዕይ በቀጣይ አጠናክሮ በማስቀጠል ዘርፉ እንዲያድግ የበኩሉን ድርሻ እንደሚወጣም አስታውቀዋል። የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ምክትል ፕሬዝዳንት ካሳሁን ተገኘ (ዶ.ር) አውደ ርዕይውና ባዛሩ የዩኒቨርሲቲውን 70ኛ ዓመት እና የሆስፒታሉን 100ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ምክንያት በማድረግ የተካሄደ መኾኑን ገልጸዋል። ዋና ዓላማው አንባቢ ማኅበረሰብ ማፍራት መሆኑንም አንስተዋል።
በአሁኑ ጊዜ ማኅበረዊ ሚዲያው መጽሐፍትን ለማንበብ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደሩንም ገልጸዋል። የማንበብ ፍቅር ላላቸው አካላት በዩኒቨርሲቲው የተለያዩ መጽሐፍት፣ የምርምር ጽሑፎች፣ መጽሔቶችና ጋዜጣዎች መኖራቸውን ገልጸዋል።
የጎንደር ዩኒቨርስቲ ቤተ መጽሐፍት ዳይሬክተር ብርቁ ገድፍ በአውደ ርዕዩ ለተማሪዎች ለጥናትና ምርምር የሚያገለግሉ የታሪክ፣ የሳይንስ እና ባሕል ነክ መጽሐፍት መቅረባቸውን ተናግረዋል። የመጽሐፍት አውደ ርዕይ መካሄዱ ለዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ብቻ ሳይሆን ለጎንደር ከተማ አንባቢያንም ጠቀሜታ እንዳለው አብራርተዋል።
በመጽሐፍት ሽያጭ ተሰማርተው ያገኘናቸው ሰዎችም የአንባቢያን ቁጥር እየቀነሰ መኾኑን አንስተዋል። ይህ የሆነበት ምክንያት የመጽሐፍት ዋጋ መጨመር ነው ብለዋል። እየተካሄደ ባለው አውደ ርዕይ ላይ መጽሐፍትን በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረቡ መኾኑን ገልጸዋል።
በመርሐ ግብሩ የመጽሐፍት ትዕይትና ሽያጭ፣ የደራሲያን ወግና ፊርማ፣ የፖናል ውይይት እየተካሄደ ይገኛል።
ዘጋቢ :- ማኅደር አድማሴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!