የችግሮችን ምንጭ ለመለየት ሕዝቡ እርስ በእርሱ እና ከመንግሥት ጋር መናበብ እና ወጥ አስተሳሰብ መያዝ ይገባዋል።

15

ወልድያ: ግንቦት 20/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የክልል እና የዞን ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ከላሊበላ ከተማ፣ ከላስታ እና ከቡግና ወረዳ ከተውጣጡ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር በወቅታዊ ጉዳይ ላይ መክረዋል። የውይይቱ ተሳታፊ አባቶች ራስን አድኖ ዓለምን ማዳን የሚያስችል መንገድ እንዳስተማሯቸው ተናግረዋል።

አሁን ግን የአባቶች መንገድ ተስቶ እና ይመሩበት የነበረው የሥልጣኔ አስተሳሰብ መንገዱ ጠፍቶ መደናበር ውስጥ መገባቱንም አብራርተዋል። በመኾኑም መንገዱ እና አቅጣጫው የት ላይ እንደተበላሸ መፈተሽ እንደሚገባም ነው ያስረዱት። የችግሮችን ምንጭ ለመለየት ሕዝቡ እርስ በእርሱ እና ሕዝቡ ከመንግሥት ጋር መናበብ እና ወጥ አስተሳሰብ መያዝ ይገባዋል ነው ያሉት ተሳታፊዎቹ።

ወንድም ወንድሙን ሲጎዳው መመልከታቸውን የተናገሩት ተሳታፊዎቹ መላው ጠፍቶባቸው መቆየቱንም ነው ያስገነዘቡት። በውሸት የመናጥ እና በሀሰት መረጃ የመደናገር ሁኔታ ነበር ያሉት ተሳታፊዎቹ አሁን ላይ ሁሉም ነገር እየጠራ በመኾኑ ችግሩ የት ላይ እንደኾነ እንደገባቸው ነው ያስረዱት።
ተሳታፊዎቹ መንግሥት ሰላም ለማጽናት የሚያከናውነውን ተግባር እንደሚደግፉ ነው ያረጋገጡት።

የሀገር ሽማግሌዎች ብቻ ሳይኾን አያንዳንዱ ሕዝብ ልጁን፣ ወንድሙን፣ እና ቤተሰቡን በመምከር ወደ ሰላም የመመለስ ሚናን መወጣት ይገባል ብለዋል። የሰሜን ወሎ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አራጌ ይመር ጫካ የገቡ ኀይሎች “የአማራን ሕዝብ ጥያቄ ልናስመልስ ነው” የሚለው መነሻቸው ማደናገሪያ እንደኾነ ተናግረዋል። ጥያቄው የሕዝብ እና የብልጽግ ፓርቲም ቁልፍ ተግባር እና አጀንዳ መኾኑ የታወቀ እንደኾነም አብራርተዋል።

የጽንፈኝነት አስተሳሰብ የወለደው የዝርፊያ ህልም ይዘው ሕዝብን እያወናበዱና እየዘረፉ ያሉ ናቸውም ብለዋል። “ችግር ካለ እንነጋገር ሲባሉ አያዳምጡም፤ ይህ ደግሞ የጽንፈኛ አስተሳሰብ ውጤት ነው” ያሉት አሥተዳዳሪው የማንነት ጥያቄው በጊዜ መልስ እንዳያገኝ እንቅፋት ኾነዋል፤ ምክንያቱም መልስ ካገኘ ሕዝብን ማደናገሪያ አያገኙም ነው ያሉት።

ስለዚህ ሕዝቡ በታጣቂው ቡድን መደናገሩን አቁሞ ችግሩን በሰላም ለመፍታት ቁርጠኛ መኾን አለበት ብለዋል። መንግሥት ዛሬም የሰላም ጥሪውን አላቋረጠም፤ ይህን ጥሪ ተቀብለው ሰላምን እንዲቀበሉ ልጆችን መምከር እንደሚገባም አሳስበዋል። ሕዝብ ማሰቃየት እና ክልሉን የማውደም ዕቅድ ይዘው በሚንቀሳቀሱት ላይ መንግሥት ሕግ ያስከብራል ብለዋል። ሕዝብም ከሰላም ጎን መቆም እንደሚገባው አስገንዝበዋል።

የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር የአደረጃጀት አማካሪ ፍስሃ ደሳለኝ ዋናው የችግሩ ምንጭ የፖለቲካ ንግድ እና የሥልጣን ጥም መኾኑንም አስረድተዋል። በዚህ መድረክ ዕውነትን መናገር ይገባል፤ የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች መሠረታችሁ እውነት በመኾኑ ይህን ሀቅ ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል።

የተናደውን ሃይማኖታዊ እና ማኅበራዊ መሠረት መገንባት እንደሚገባም ጠቁመዋል። የሚፈፀምን ዘግናኝ ድርጊት ልታወግዙ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል። ጽንፈኞች በፈፀሙት ዘግናኝ ድርጊት ከንፈር ከመምጠጥ ባለፈ የችግሩን ምንጭ በሀቅ ተረድተን በትብብር መፍትሔ ማበጀት አለብን ነው ያሉት። የቅዱስ ላሊበላን እና የቀደሙ አባቶችን ጥበብ ተጠቅማችሁ የአካባቢያችሁን ሰላም ለማጽናት በቁርጠኝነት ሥሩ ሲሉም አሳስበዋል።

የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን(ዶ.ር)፣ የርእሰ መሥተዳድሩ አደረጃጀት አማካሪ ፍስሀ ደሳለኝ፣ የሰሜን ወሎ ዞን አሥተዳዳሪ አራጌ ይመር እና የሰሜን ምሥራቅ እዝ ምክትል አዛዥ ሜጄር ጄኔራል ሻምበል ፈረደ በምክክሩ ተገኝተዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየዝንጀሮ ፈንጣጣ በሽታ በሀገሪቱ እንዳይስፋፋ በትኩረት እየተሠራ መኾኑን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።
Next articleየጎንደር ዩኒቨርሲቲ የንባብ ባሕልን ለማሳደግ የበኩሉን ድርሻ እንደሚወጣ አስታወቀ ።