
አዲስ አበባ: ግንቦት 20/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የጤና ሚኒስቴር የዝንጀሮ ፈንጣጣ በሽታ ያለበትን ደረጃ በሚመለከት ለመገናኛ ብዙኀን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል። የጤና ሚኒስትሯ መቅደስ ዳባ (ዶ.ር) በተለምዶ የዝንጀሮ ፈንጣጣ እየተባለ የሚጠራው የኤም ፖክስ በሽታ በአሁኑ ወቅት የአፍሪካ ብሎም የዓለም የጤና ስጋት ተብሎ በዓለም ጤና ድርጅት መፈረጁን አንስተዋል።
እንደ ጤና ሚኒስትሯ ገለጻ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከጥር 2022 እስከ ሚያዝያ 2025 ባለው ጊዜ ድረስ 142 ሺህ ዜጎች በኤም ፖክስ በሽታ የተያዙ ሲኾን 328 የሚኾኑት ደግሞ ለህልፈት መዳረጋቸውን የዓለም የጤና ድርጅት ባወጣው ሪፖርት ማረጋገጥ ተችሏል። በአፍሪካ አህጉር ብቻ ካለፉት ሦስት ዓመታት ጀምሮ እስካሁን በ29 የአፍሪካ ሀገራት የተከሰተ ሲኾን ከ38 ሺህ በላይ ሰዎች በበሽታው ተይዘዋል ነው ያሉት። 146 ያህሉ ደግሞ ለህልፈት ተዳርገዋል ብለዋል።
ባለፉት አምስት ወራት የበሽታው ስርጭት 78 በመቶ መጨመሩንም ሚኒስትሯ ገልጸዋል። በተለይም በአፍሪካ አህጉር በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ በኡጋንዳ እና በቡሩንዲ በከፍተኛ መጠን መከሰቱን ነው የተናገሩት። ጎረቤት ሀገር ኬኒያ እና ደቡብ ሱዳንም በበሽታው የተያዙ ሰዎችን አስመዝግበዋል ብለዋል። በኢትዮጵያም በሞያሌ ከተማ አካባቢ ግንቦት 17/2017 ዓ.ም በተደረገው የላብራቶሪ ምርመራ በሽታው በ21 ቀን ህጻን ላይ መከሰቱን በመግለጫቸው አንስተዋል።
በሽታው የተላለፈው ከአባትየው መኾኑ የተረጋገጠ ሲኾን አናቱም መያዛቸው ተረጋግጧል ነው ያሉት። ይሁን እንጅ የሦስቱም የጤና ሁኔታ በጥሩ ደረጃ ላይ ይገኛል ብለዋል። አሁንም በአካባቢው ተጨማሪ የናሙና ሥራዎች እየተሠሩ እንደኾነ ነው የገለጹት። በሽታው ከጎረቤት ሀገር እንዳይዛመት በአጎራባች አካባቢዎች የቁጥጥር፣ የቅኝት እና የክትትል ሥራዎች እየተከናወኑ እንደኾነም ተናግረዋል። በተለይም ተጋላጭነት ባለባቸው በኦሮሚያ፣ በሱማሌ እና በደቡብ ክልል መግቢያና መውጫ በሮች ላይ የቅኝት እና የልየታ ሥራዎች እየተከናወኑ እንደኾነ ነው የገለጹት።
የተለያዩ የኅብረተሰብ ጤና አደጋዎችን የቅድመ ዝግጅት፣ የቅኝት እና የምላሽ እንዲሁም የድንበር አካባቢዎች ጤና ልየታ እና አገልግሎት ሥራዎችን የኅብረተሰብ ጤና አደጋዎች ማስተባበሪያ እና ምላሽ ማዕከል በማቋቋም እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡ አሁን ላይ እንደ ሀገር የበሽታው የስርጭት ደረጃ ዝቅተኛ ነው ያሉት ሚኒስትሯ በሽታው እንዳይስፋፋ የተጀመረው ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።
ሳል፣ በሰውነት ላይ የሚወጣ ሽፍታ፣ ትኩሳት፣ የራስ ምታት፣ የዕጢ እብጠት፣ የቆዳ ቁስለትና ድካም፣ የጡንቻ እና የጀርባ ህመም ዋና ዋና የበሽታው ምልክት እንደኾኑም ጠቁመዋል። የተጠቀሱትን ምልክቶች የሚያሳይ ማንኛዉም ሰዉ በሚገኝበት ጊዜ በአቅራቢያ ወደሚገኝ የጤና ተቋም በመሄድ የምርመራ እና የሕክምና አገልግሎት ማግኘት ይኖርበታል ነው ያሉት። በተጨማሪም በ952 እና 8335 ነጻ የስልክ መስመር ጥቆማ ማድረስ እንደሚገባ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ዘጋቢ: ቴዎድሮስ ደሴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!