ከ1 ሺህ 300 በላይ ተማሪዎች የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ፈተናን በበይነ መረብ እንደሚወስዱ የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ገለጸ።

22

ደብረ ብርሃን: ግንቦት 20/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ስር ከሚገኙ 10 የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ 1ሺህ 965 ተማሪዎች የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ፈተና እንደሚወስዱ የከተማ አሥተዳደሩ ትምህርት መምሪያ ገልጿል። የሀገር አቀፍ ፈተናውን ከሚያስፈትኑ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ስድስት ትምህርት ቤቶች ፈተናውን በበይነ መረብ እንደሚያስፈትኑ ነው የተገለጸው።

ተማሪዎቹን ለፈተናው ለማዘጋጀትም ሲባል በከተማ አሥተዳደሩ ደረጃ የተዘጋጀ ሞዴል ፈተና በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ በበይነ መረብ እየተሰጠ ይገኛል። ሞዴል ፈተናውን ስትወስድ አሚኮ ያገኛት የደብረ ብርሃን አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የማኅበራዊ ሳይንስ ተማሪ እመቤት መኩሪያ በትምህርት ቤታቸው ልምምዶችን ሲያደርጉ መቆየታቸውን ተናግራለች። ይሁን እንጅ ከዚህ በፊትም በሞዴል ፈተናው ላይ የኢንተርኔት መቆራረጥ እና የኮምፒውተር ችግሮች እንደተስተዋሉ ነው የጠቆመችው።

የኃይሌ ማናስ አካዳሚ የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪ ቢልልኝ እሸቱ በበኩሉ ትምህርት ቤታቸው ከ9ኛ ክፍል ጀምሮ በበይነ መረብ የተደገፈ ተግባር ተኮር ሥልጠና ሲሰጣቸው እንደቆየ ገልጿል። በሞዴል ፈተናው ላይ የኮምፒውተር እጥረት፣ የኢንተርኔት ፍጥነት ችግሮች እንዲሁም በአንዳንድ ተማሪዎች ላይ የኮምፒውተር ክህሎት ችግሮች በመስተዋላቸው ለዋናው ፈተና ከዚህ ከፍ ያለ ዝግጅት ያስፈልጋል ብሏል።

የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ኀላፊ መቅደስ ብዙነህ 1ሺህ 390 ተማሪዎች ሀገር አቀፍ ፈተናውን በዲጅታል ታግዘው ይወስዳሉ ብለዋል። ከደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ እና ከሌሎችም አጋር ተቋማት ጋር በመተባበር ተማሪዎቹን ለማብቃት በርካታ ሥራዎች ሲሠሩ እንደቆዩም ኀላፊዋ አብራርተዋል።

የበይነ መረብ አጠቃቀም ላይ የክህሎት ችግር እንዳያጋጥማቸው እና ተግባር ተኮር ልምምድ እያደረጉ ስለመኾኑም ነው የጠቆሙት። የሞዴል ፈተናው ትምህርት የምንወስድበት ነው ያሉት መምሪያ ኀላፊዋ መቅደስ ብዙነህ በሞዴል ፈተናው ላይ የተስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ እንሠራለን ነው ያሉት።

የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ጌትነት አሸናፊ (ዶ.ር) ዩኒቨርሲቲው ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ የተለያዩ ፈተናዎችን በበይነ መረብ የማስፈተን ልምድ አለው ብለዋል። ሀገር አቀፍ ፈተናው በሁለት ዙር ስለሚሰጥ በሞዴል ፈተናው ላይ ያጋጠሙ አንዳንድ የቴክኒክ ችግሮች እንደሚስተካከሉም ተናግረዋል።

በቂ የቴክኒክ ድጋፍ ሰጭ ባለሙያዎች አሉን ያሉት የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንቱ በቂ ዝግጅትም ተደርጓል ብለዋል።

ዘጋቢ፦ ሥነ ጊዮርጊስ ከበደ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous article“የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሀገር ግንባታ ተገቢውን አስተዋጽዖ እንድታበረክት መንግሥት የሚጠበቅበትን ሁሉ ይወጣል” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
Next articleየዝንጀሮ ፈንጣጣ በሽታ በሀገሪቱ እንዳይስፋፋ በትኩረት እየተሠራ መኾኑን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።